የመጀመሪያው የአፍሪካ ፈጠራ ሳምንት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው

2322

አዲስ አበባ ጥቅምት 17 /2012  በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የአፍሪካ ፈጠራ ሳምንት በአዲስ አበባ አፍሪካ ህብረት ውስጥ እየተካሄደ ነው።

የፈጠራ ሳምንቱ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከአይ ቢ ኤ ሴንተር ፎር ኢኖቬሽን፣ አፍሪካ ኅብረት ኮሚሽንና ከኦስሎ ኢንተርናሽናል ሃብ ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው።

ለአንድ ሳምንት በሚቆየው የፈጠራ ሳምንት ላይ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ከ200 የአፍሪካ አገሮች የተውጣጡ የፈጠራ ባለሙያዎች እየተሳተፉበት ነው።

በሴቶችና ስራ ፈጠራ፣ ግብርና፣ በጤና፣ በቱሪዝምና መስተንግዶ፣ በከተማ ኑሮ፣ ንግድና ኢንቨስትመንት ላይ የሚያተኩሩ የፈጠራ ስራዎችም ቀርበዋል።

የፈጠራ ባለሙያዎች እርስ በርስ ትስስር እንዲፈጥሩ ከማድረግ ባለፈ ከኢንቨስተሮች ጋር በማገናኘት ሁኔታዎችን ማመቻቸት ከሳምንቱ ከሚጠበቁ ዓላማዎች መካከል የሚጠቀስ ነው።

የፈጠራ ሳምንቱ የአፍሪካ አህጉር ፖሊሲ አውጪዎች፣ ተመራማሪዎች፣ ባለሃብቶችና ዓለም አቀፍ ተቋማት የሚሳተፉበት ሲሆን በፈጠራ የታገዘ ልማት ለማምጣት አወንታዊ ሚና እንዳለው ተገልጿል።

የአፍሪካ ኀብረት ኮሚሽን አፍሪካን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወትና በአጀንዳ 2063 ወደብልጽግና ለመሸጋገር የተያዘውን ውጥን በእጅጉ እንደሚያግዝ እምነት እንዳለው ተጠቁሟል።

”ሳምንቱ ትልቅ የኢኮኖሚ እድል የያዘ ነው” ያለው ኮሚሽኑ፤ አዳዲስ የገበያ አማራጮችን የያዘና በዘርፉ የባለኃብቶችን ተሳትፎ የሚያበረታታ መሆኑን ጠቁሟል።

የሳይንስና ኢኖቬሽን ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ እንደገለጹት፤ አፍሪካውያን መስተጋብራቸውን የሚያጠናክሩበት መሰል መድረክ በድህነት ቅነሳ፣ የኑሮ ደረጃ ማሻሻልና የበቃ ማህበረሰብን እውን ለማድረግ የላቀ ፋይዳ አለው።

አፍሪካ በቴክኖሎጂና ፈጠራ ዘርፍ ዓለም የደረሰበት ደረጃ ለመድረስ በስመኩ ብዙ መስራት እንደሚጠበቅባት የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ”እያደገ የመጣውን የአህጉሩን የሕዝብ ቁጥር የሚመጥን የስራ ዕድል ፈጠራ ላይ በትኩረት መሰራት አለበት” ብለዋል።

የቴክኖሎጂ ዘርፍ ለወጣቶች የስራ ዕድል የመፍጠር አቅም እንዳለው አመልክተው፤ መንግሥታት በመስኩ ለሚካሄዱ ጥናቶች በጀት መድበው የቴክኖሎጂ ማፍለቂያ ማእከላት እንዲገነቡና የሰው ኃይል እንዲያለሙ ጥሪ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ የፈጠራ ስራዎች እንዲበረታታና የሚፈለገው ውጤት እንዲመጣ ከአፍሪካ ህብረቱ አባል አገሮችና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በቅንጅት ለመስራት ቁርጠኛ መሆኗንም አረጋግጠዋል።

በኢትዮጵያና ጂቡቲ የኖርዌይ አምባሳደር ሜሬት ሊንዴሞ ፈጠራ በተለይም የአረንጓዴ ኢኮኖሚ እንዲጎለበት ከፍተኛ ሚና ያለው በመሆኑ ዘላቂ የልማት ግቦች እንዲሳኩ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።

የቴክሎጂ ፈጠራዎች የእውቀት ልውውጥ፣ የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠትና የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ሁነኛ መንገድ መሆኑን አመልክተዋል።

እንደ አምባሳደር ሜሬት ገለጻ፤ ኖርዌይ በአፍሪካ የዲጂታል እንቅስቃሴ እንዲጠናከር የሙያ ድጋፍ ታደርጋለች።

በቴክኖሎጂ ሳምንቱ ላይ ከኢትዮጵያውያን የፈጠራ ባለሙያዎች በተጨማሪ ከናይጄሪያ፣ ቶጎ፣ ኡጋንዳ እንዲሁም ኬኒያ ባለሙያዎ እየተሳተፉ ነው።

በመርሃ ግብሩ ማጠቃለያ ላይ ለፈጠራ ውድድር አሸናፊዎች የብር ሽልማት እንደሚሰጥ ታውቋል።

በዚሁ መሰረትም ለ50 ተወዳዳሪዎች ለእያንዳዳቸው 1 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ሽልማት የሚበረከት ሲሆን የመጨረሻውን ሽልማት የሚያሸንፉ አምስት ተወዳዳሪዎች ደግሞ አምስት ሺህ የአሜሪካን ዶላር ይሸለማሉ።