በአዋሽ ወንዝ ላይ በደረሰ የታንኳ መገልበጥ የጠፉ የስድስት ሰዎች አስከሬን ተገኘ

75
አዳማ ሰኔ 12/2010 የአዋሽ ወንዝን በማቋረጥ ላይ የነበረችው ታንኳ በመገልበጧ ምክንያት ጠፍተው የነበሩ ስድስት ሰዎች ከ56 ሰዓታት ፍለጋ በኋላ የሁሉም አስከሬን  መገኘቱን  ፖሊስ ገለፀ ። ታንኳዋ 18 ሰዎችን አሳፍራ የአዋሽ ወንዝን በማቋረጥ ላይ እንዳለች የወንዙ  የውሃ ፍሰት በመጨመሩ  ምክንያት ቅዳሜ ሰኔ 9 ቀን 2010 ዓ.ም ከረፋዱ አራት ሰዓት አካባቢ ተገልብጣ  ነበር ። በአካባቢው ህብረተሰብና በዋናተኞች ርብርብ  የ11 ሰዎች ህይወት ማትረፍ ሲቻል የአንዲት እናት አስከሬን በእለቱ መገኘቱን አስታውሰዋል፡፡ ሌሎች ስድስት ሰዎች  ወንዝ ውስጥ ገብተው መጥፋታቸውን ፖሊስ በወቅቱ መግለፁ ይታወሳል ። የወንጂና የዝዋይ ዋናተኞች ፣ የፀጥታ ሃይሎች ፣ የወንጂ አካባቢ ህብረተሰብና የጠፉት ሰዎች ቤተሰብ አባላት ለ56 ሰዓታት ያክል በአዋሽ ወንዝ ያደረጉት እልህ አስጨራሽ ፍለጋ ትናንት ከቀኑ 12 ሰዓት አካባቢ የሁሉንም አስከሬን በማግኘት መጠናቀቁን የምስራቅ ሸዋ ዞን ፖሊስ የህዝብ ግንኝነት ኃላፊ ኮማንደር አስቻለው ዓለሙ ለኢዜአ  ገልፀዋል ። ታንኳዋ በተገለበጠችበት ቅፅበት ህይወቷ ያለፈውና አስከሬኗ ወዲያውኑ የተገኘው  እናት  ከጎኗ በታንኳዋ ተሳፍሮ የነበረው የ11 ዓመት ልጇ በህይወት ተርፏል ። በአደጋው ጠፍተው ትናንት አስከሬናቸው ከተገኘው 6 ሰዎች መካከልም አራቱ የአንድ ቤተሰብ አባላት መሆናቸውን ፖሊስ በወቅቱ አሳውቆ ነበር፡፡ የሞቱት ሰዎች አስከሬን ለቤተሰቦቻቸው የተሰጠ ሲሆን ቀብራቸውን ዛሬ  እንደሚፈፀም ኮማንደር አስቻለው አስታውቀዋል ። ኮማንደሩ  የጠፉትን ሰዎች በመፈለግና አስከሬናቸውን በማውጣት ርብርብ ላደረጉት ዋናተኞች ፣ ለፀጥታ ሃይሎች ፣ ለመስተዳድር አካላትና ለአካባቢው ህብረሰብ   ምስጋና አቅርበዋል ።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም