ለነገ ስኬት የዛሬ ትዕግስት

73

ሀብታሙ ገዜ (ድሬዳዋ ኢዜአ)

በገንደ ተስፋ አካባቢ ተወልዶ አደገ የራሱን ትዳር በመመስረትም የአባወራነትንና የልጅ አባትነትን ጸጋ አገኘ። የድሬዳዋ ከተማው ነዋሪ ኤልያስ መሐመድ ልዩነቶች ውበት፤ ቋንቋዎች ልዩ ሃብት ሆነውት እድሜውን ሙሉ በዛው እንዳሳለፈም ይናገራል።

የከተማው ነዋሪዎች ለፍቅርና ለመዋሃድ ስሱ ናቸው ፤የሚፈጥሩት ምትሃታዊ ድባብና የሚለግሱት ልዩ አክብሮት ባይተዋርን ጎትቶ ያለምዳል፤ አላምዶ ያስቀራል፡፡አሁን ላይ “ነበር” ለማለት የሚከጅላቸው እንዳሉ ሳይዘነጋ።

ነዋሪዎቹ ልዩነት ሣይገድባቸው ሃዘንና ደስታን ተገማምደው ኖረውታል፡፡ የሚፈጠርን ልዩነት በመወያየት ያቀሉታል፤ መፍትሄም ይሰጡታል፤ የትኛውንም የኃይማኖት ተቋማት በጋራ ያንፃሉ።ይሔ የድሬዎች የዘመናት አብሮነት መገለጫ ነው።

ታህሳስ 15/1895 ዓ.ም.ከወደ ጅቡቲ ወደሷ የገባው ባቡር እንደ ከተማ እንድትመሰረት በምክንያትነት የሚጠቅሱት ብዙዎች ናቸው፤በአናቱ ህብረ-ብሔራዊነት እንዲያብብ የተለያዩ የውጭ ሀገራት ዜጎች ለዘመናት መኖራቸው የህብረተሰቡን ጉራማይሌነት እንዲጎላም አድርጎታል።

አብሮነት ሁሉን ነገር በጋራ መከወን በድሬ ብርቅ አይደለም፣ድሬ-የአብሮነት የአንድነት የሰላም የፍቅር እውነተኛ ከተማ ነበረች ይህ ማንነቷ በሀገሪቱ አራቱ ማዕዘናት የናኘና የተጣጣመ መሆኑ ብዙዎች የሀገሪቱ ዜጎች ለከተማዋ ልዩ ፍቅርና አክብነሮት እንዲኖራቸው አድርጓል፡፡

የዚህች ከተማ ፍሬ በመሆኑ የሚኮራው ወጣት ኤሊያስ የእሱና የጓደኛው እናቶች አንዳቸው የሌላኛቸውን ልጅ ጡት እያጠቡ፣ አንዳቸው በቤት ሲኖሩ ሌላኛዋ የመንከባከብን ኃላፊነት እየወሰዱ እንዳሳደጓቸው ይናገራል።

አሁን ትዳር መስርቶ የአንድ ልጅ አባት የሆነው ኤልያስ "እኔ በአባቴ ኦሮሞ.በእናቴ አፋር፤ ባለቤቴ ደግሞ ሶማሌ ናት፤ ልጄ ወደፊት የየትኛውን ብሔር ተወላጅ እንደምታገባ አላውቅም፤ እህል ውሃዋ የፈቀደውን እንጂ፤ ድሬ የተደመረ ቤተሰብ፤ ህብር የፈጠሩባት ከተማ ናት" ይላል።

ይህ ታላቅ ገጽታና ልዩ መገለጫ ባለፉት ዓመታት ባልተገባ መንገድ በመጓዙ ችግር ላይ ወድቋል፤ ያ ቀድሞ ድሬ የምትታወቅበት የአብሮነትና የሁሉን ተቀባይነት ልምዷ ስጋት እያጠላበት የህመም ምልክቶች የሆኑ አንዳንድ ተግባራት መታየት ጀምረዋል።

ነዋሪዎቿም ከክፍለ ዘመን በላይ ቤታቸው መዲናቸው የሃገር የመደመር ተምሳሌቷ ፣የአንድነት መገለጫዋ ድሬ እየታመመች መምጣት አሳስቧቸዋል።አሁን አሁን ለሚፈጠሩ ችግሮች መፍትሄ ፍለጋ የሚደረጉ ውይይቶችና ስምምነቶች ሳይቀሩ እንዲሰናከሉ የሚተጋም እንዳለ እየተስተዋለ ነው።

"የተሳሳቱ መረጃዎችን ቆም ብሎ ማስተዋል ጠፍቷል፤ በተንቀለቀለ የእሳት ጎርፍ ውስጥ ገብቶ እሳቱን የሚያራግብ፣ ባልነበረና ባልተፈጠረ አሉባልታ የሚታመስም አልጠፋም፤ ሁከትና ብጥብጡ መሠረት የለውም፣ ጊዜያዊ የፖለቲካ ወላፈን የፈጠረው ህመም ነው" ይላል ኤልያስ

በቀዳሚው ሳምንት ለምረቃ የበቃው የጠቅላይ ሚኒስትሩ መጽሐፍ የድሬዳዋን የቀድሞ መገለጫ መልሶ እንዲፀና መድኃኒት ይሆናል የሚል እሳቤ በነዋሪዎቿ ዘንድ እየታየ ነው፡፡የድሬዳዋ የዘመናት የህይወት ዘይቤ ባህላዊ መገለጫዎች ከሳይንሱ ተዳቅሎ ሀገራዊ ቃና እንዲኖረው መሰነዱ ለሀገር ህመም ጭምር ፈውስ እንደሚያመጣም ተስፋ ሰንቋል፡፡

በሀገራችን ልዩነቶች ውበቶች ፤ክልሎች ጌጦች፤ ህብረትና መደመር ፈርጥ ይሆናል፤በአናቱ የመደመር መርህ መተግበር የሀገርን መጻኢ ዕድል ብሩህ ያደርጋል የሚሉት ደግሞ ሌላው የድሬ ነዋሪ አቶ አብይ ዘርጋው ናቸው፡፡ መፅሐፉን የገዛው ሁሉ በአግባቡ አንብቦ ለሌላው ቢያስረዳ ለድሬዳዋ ብቻ ሣይሆን እንደሀገርም የሚጠቅም መድሃኒት እንዳለው ያስረዳሉ።በተለይ በመንግስታዊ ተቋማት ጊዜ፣ እውቀት ፣በጀት እንደውሃ ሲፈስባቸው በነበሩት እንደ ቢኤሰሲ፣ ቢፒአርና የመሳሰሉት አሰራሮች ላይ መልካም ነገር የሚያመጣ እንደሆነም ተናግረዋል።

"መደመር መጨፍለቅ ለማምጣት ታስቦ ነው እያሉ የተሳሳተ አሉባልታ የሚነዙት በፖለቲካው የከሰሩ ፣ በሥልጣን ሲያጋብሱት የነበረውን ሃብት የተነፈጉ አካላት አጀንዳ ነው" የሚሉት ደግሞ የድሬዳዋ የካቢኔ አባልና የከተማ አስተዳደሩ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር ጀማል ኢብራሂም ናቸው።

"መደመር አዳጊ ክልሎችን አጋር ድርጅቶች በሚል የዳቦ ስያሜ ላለፉት 27 ዓመታት በሀገር ጉዳይ ላይ ሲገለሉ ለነበሩት መፍትሄ ይሰጣል፤ በልማት አጀንዳ ላይ ለተረሱት አርብቶ አደሮች ትኩረት የሚሰጥም ይሆናል፤ ሁሉም ክልሎች በሃብታቸው እውቀታቸውና በጀታቸው ያለሞግዚት አስተዳዳሪዎች እውነተኛ ክልል ሆነው ለአንድነትና ለህብረት ትልቅ አበርክቶ እንዲኖራቸው ያስችላል" ይላሉ ፡፡

"በመፅሐፉ የተካተቱ መሠረታዊያንን በየደረጃው ለሚገኙ ዜጎችና አመራሮች ማስረዳት ቀጣዩ ሥራችን ይሆናልም" ብለዋል፡፡

መምህር ኤፍሬም በዛብህ መፅሐፉ ሀገሪቱ የምትመራበትን መሠረታዊ መርህ ያካተተ፤ ማህበራዊ፣ የምጣኔ ሃብትና የፖለቲካ ህመሞች መፍትሄዎችን የጠቆመ መሆኑ ጥሩ ነው፤ ግን አሁንም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሁራንና ሊቃውንት ሊተችና ሊዳብር እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡

መደመርን አስመልክቶ ለሀገር በሚያስቡም ሆነ ሀገር የሚያፈርሱ ፅንፍ አንግበው የሚንቀሳቀሱት የፖለቲካ ድርጅቶችና የአክቲቪስቶች ድምፅ ጭምር ቢደመጥ መልካም እንደሆነም መክረዋል፡፡

ለእኔ መደመር ያነገባቸው ባህላዊ እሴቶች ድሬዳዋን ይገልፃል ያሉት ደግሞ አቶ ነቢል መሐመድ ናቸው፡፡

"ድሬዳዋ በኃይማኖት ፣በብሔር፣በጎሳ፣በቋንቋ መቧደን የሌለባት ንፅህናና እውነት የነገሰባት ከተማ ናት፤

አሁን እንኳን ነበረች ወደ ማለቱ እየተገፋች ነው፡፡ ነገር ግን በመደመር የተገነባው የድሬ ማንነት መደመር መፅሐፍ ይዟቸው በተነሳው ቁም ነገሮች ይመለሳሉ የሚል ተስፋ አለኝ" ይላሉ።

"የቤተሰቤን ጉራማይሌና ድንቅ ህብር ላጫውትህ፤ እናቴ ኦርቶዶክስ፣ አባቴ ሙስሊም ፤ ባለቤቴ ካቶሊክ፤ አባቴ ኦሮሞ፣ እናቴ አማራ፣ ወንድሜ ፕሮቴስታንት ሚስቱ ሶማሌ ፣ የኔን ልጅ አላውቅም" ይላሉ የሶስተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ የሚገኙት መምህሩ።ይህን ዓይነት ድንቅ መስተጋብር በድሬዳዋ በብዛት እንዳለ ጠቁመው ሰው በመሆን በመብሰል የሚገኝን ድንቅ ፀጋ መጠበቅና ሊንዱት ከሚፈልጉ አካላት መከላከል የሁሉም ኃላፊነት ሊሆን እንደሚገባም ይመክራሉ።

የሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋቹ በወጣትነት ዕድሜው ከሃረማያ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ለመከታተል ድሬ ላይ ይከትማል፤ አቶ አብዱል ሰመድ አህመድ። "ከትምህርት ቤት ስንለቀቅ የተሻለ ኑሮ የሚኖሩ ቤተሰቦችን ጊቢ ማንኳኳት ነው፤ ያነኳኳንበት ቤተሰብ የሚበላውን ዓይነት ምግብ በትሪ ሞልቶ በር ላይ ይመጣል፤ ማነህ ፣ከየት፣ ወደ የት ነህ የሚል የለም፤ ሰው መሆንህ በቂ ነው፤ ያስተማረኝ የተደመረው ውቡ የድሬዳዋ ህዝብ ነው" ይላል በትዝታ ተጉዞ ፡፡

"ያ እኛ አጣጥመን የቀመስነው የአኗኗር ዘይቤ እየተበላሸ መሆኑ አሳዝኖኛል፤ ሣይቃጠል በቅጠል እንዲሉ ፈጣን መፍትሄ ሊበጅለት ይገባል" ሲል በቁጭት ይናገራል።

የመደመር ማሳያ በሆነችው ድሬ ላይ መጽሃፉ በተመረቀበት ወቅት የሃይማኖት አባቱ ሊቀ ብርሃናት ቀለመወርቅ ቢምረው ስለ ከተማይቱ የቀድሞ ማንነት ዳግም መመለስ ሲናገሩ "ልጆቻችን አሁንም አልተጣሉም፤ አልተለያዩም፤ ሁሉም ራሱን ይመርምር!! የተለያየች መንግስት አትፀናም" በሚል ከሃይማኖታዊ አስተምህሮውን ጠቅሰው ገልጸዋል።መጽሐፉም የወደፊት መልካም ነገሮችን ይዞ እንደመጣ ያላቸውን ተስፋ በመጠቆም። "መፍትሄው የተመሰረተው የነበረውን ፍቅርና አንድነት መጠበቅ ላይ ነው፤ ከዚህ ውጭ የሰላም እጦት ስደት ፤ ሞት፤ ህመም፤መበተን ብቻ ነው" ሲሉ በአጽንኦት አሳስበዋል፡፡

በዚሁ የመጽሐፍ ምረቃ መድረክ ላይ የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪዎች መደመርን በተግባር እየኖሩት መሆናቸውን በምሳሌነት ያስረዱት የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ኦዲፒ ኮሚቴ አባል ዶክተር አለሙ ስሜ የተናገሩትም የከተማይቱ ነባራዊ ሁኔታ ማሳያ ነው።በወቅቱ እሳቸው አንድ ነገር አሳስበው ነበር ፤እሳት በመለኮስ የርስ በርስ መተላለቆች እንዲፈጠር ቀን ከሌት የሚሰሩ ሰዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል መንግስትና ህዝብ በጋራ መስራት መስራት እንደሚገባ!

ትክክል ነው ከመገዳደል ፤ከመገፋፋት፤ ከመጠላላት የሚያተርፍ ማንም የለም ከሩዋንዳ፤ከፍሲልም ከየመንና ከሶሪያ መማር ብልህነት ነው፡፡ የሞትን አስከፊነት ለማወቅ ሞቶ መሞከር አይጠበቅም መደመር መተባበር መረዳዳት የጥንቱን የድሬ አብሮነት ማስቀጠል ብቸኛው አማራጭ እንደሆነ በማመን በየአካባቢው ያለውን ትኩሳት በሰከነ መንገድ ለመፍታት መትጋትን ወቅቱ የሚሻው አብይ ጉዳይ መሆኑን ልብ ይሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም