በሩሲያ ምድር ስለኢኮኖሚ ትብብር የመከረው መድረክ

98
ጥቅምት 15/2012 በጥቁር ባህር ዳርቻ በምትገኘው የሩሲያ ሶቺ ከተማ አፍሪካና ሩሲያ የትብብራቸውን አድማስ ለማስፋት ቃል የተገባቡበት መድረክ ሲካሄድ ከተለያዩ አገሮች የተገኙ ሶስት ሺ ያህል የልዑካን ቡድን ተሳትፈዋል። ይሄው ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው የሩሲያ - አፍሪካ ትብብር መድረክ ለሁለቱም ወገኖች መልካም ነገርን ሰንቋል። የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከአፍሪካ ጋር በትብብር እንደሚሰሩ በመድረኩ ላይ መናገራቸው ለዚህ ዋነኛ ማሳያ ነው። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት እስከአሁን ድረስ የሩሲያና አፍሪካ የንግድ ልውውጥ በጣም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። የመድረኩ መካሄድና ከግዙፍ የኩባንያ ባለሀብቶች ጋር ጎን ለጎን መወያየታቸ መጪው ጊዜን ለመጠቀም የሚያስችል በር ከፋች ነው። በዚህ ሳምንት አጋማሽ ላይ በሶቺ ከተማ የተካሄደው የሩሲያ አፍሪካ የትብብር መድረክ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ጨምሮ ከ30 በላይ የሚሆኑ የአፍሪካ አገሮች መሪዎች፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት ሃላፊዎችንና ባለሃብቶች ተሳትፈዋል። መድረኩ በዋናነት በሩሲያና አፍሪካ መካከል የምጣኔ ሃብትና መሰረተ ልማት ትብብርን ለማጠናከር ያለመ ነው። በተለይም በሩሲያና በአፍሪካ አገሮች መካከል በጋራ የሚከናወኑ የግብርና፣ የሰፋፊ ኢንዱስትሪዎች፣ ጤና እና ትምህርትን ይበልጥ ለማጠንከር የሚያስችሉ ፕሮጀክቶች የወደፊቱን አቅጣጫ ያመላከቱ ናቸው። በመድረኩ ኢትዮጵያ "አገራዊ ጥቅሟን ያስጠበቀ የዲፕሎማሲ ተግባራትን" ለማከናወን የቻለች ሲሆን፤ ከሩሲያም የዕዳ ስረዛ ተደርጎላታል። በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተመራው የልዑካን ቡድን ከመድረኩ ጎን ለጎን የተለያዩ ተግባራት አከናውኗል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲንና የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበር አብዱል ፈታ አልሲሲ በመሩት የመሪዎች መድረክ ላይ ንግግር አድርገዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው በሁሉም የዓለማችን ጫፍ እየታዩ ያሉ ውስብስብ ችግሮችን መፍታት "የምንችለው ከተባባበርን ብቻ ነው" ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። የዜሮ ድምር ጨዋታ ትብብሮች ዓለምን ከፍተኛ ዋጋ እንዳስከፈላትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጽንኦት ሰጥተውታል። የኢትዮጵያ መንግስት ትብብር ያለውን ፋይዳ በመረዳቱ "በመደመር እሳቤ" ከአገር ባለፈ ቀጣናውን ለማስተሳሳር እየሰራ መሆኑንም ነው የገለጹት። መደመር 'ያለፉ መልካም እሴቶችን ማስፋት፤ ዛሬ ላይ ገቢራዊ ማድረግና ለመጭው ትውልድ የተደራጀ ካፒታልን ማሸጋገር' የሚሉ እሳቤዎች እንዳለውም ለተሳታፊዎቹ አስረድተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ከመድረኩ ጎን ለጎን ከፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ምክክር አድርገዋል። ፕሬዚዳንቱ በዚህን ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰላም ኖቤል ተሸላሚ መሆናቸውን አድንቀው፤ በሩሲያና ኢትዮጵያ መካከል ያለው ትብብር ይበልጥ እንዲጠናከር ጥሪ አቅርበዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ስላለው አጠቃላይና በተለይም የኢኮኖሚ ሪፎርም ለፕሬዚዳንቱ አብራርተውላቸዋል። መንግስታቸው በቀጣይ አስር ዓመት ኢትዮጵያን ግዙፍ ኢኮኖሚ ካላቸው አምስት የአፍሪካ አገሮች ተርታ ለማሰለፍ እየሰራ መሆኑን በመግለጽ። ሁለቱ መሪዎች በምክክራቸው በመሰረተ ልማት፤ ትምህርትና ግብርና ዘርፎች ተደጋግፈው ለመስራት ስምምነት ላይ ደርሰዋል። ኢትዮጵያ የኒኩሌር ሃይልን ለሰላማዊ ልማት ለማዋል በምታደርገው ጥረት ከሩሲያ ድጋፍ እንድታገኝ የሚያስችላትን ስምምነት መፈራረሟ ደግሞ ለአብነት ተጠቃሽ ነው። በኢትዮጵያ ወገን ስምምነቱን የተፈራረሙት የሳይንስና ኢኖቬሽን ሚንስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ከሶስት እስክ አምስት ዓመት የኒኩሌር ሃይል ምርምር ጣቢያ ትገነባለች። በስምምነቱ መሰረትም ኢትዮጵያ እቅዷን ለማሳካት ከሩሲያ የቴክኖሎጂ ድጋፍ እንደምታገኝ ነው የተናገሩት። የምርምር ተቋሙ በካንሰር ህክምና ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራም ተብራርቷል። በኒኩሌር ኢነርጂን ለሃይል ልማት ማዋልም ሌላኛው የስምምነቱ ማዕቀፍ መሆኑንም ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን ያመለከቱት። የኒኩሌር ኢነርጂ ከአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ ነጻ የሆነ የሃይል ልማት መገንባት እንደሚያስችል በመጠቆም። የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሪታሪያት ሃላፊው አቶ ንጉሱ ጥላሁን በበኩላቸው እንደሚሉት፤ ሩሲያ ለኢትዮጵያ የ163 ነጥብ5 ሚሊዮን ዶላር የብድር ስረዛ አድርጋለች። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከመድረኩ ጎን ለጎን የሁለትዮሸ ውይይት ያደረጉ ሲሆን፤ ከግብጹ መሪ አብደል ፈታ አል ሲሲ ጋር ምክክር አድርገዋል። የምክክሩ ዋነኛ ማጠንጠኛ የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ሲሆን፤ አገሮቹ ጉዳዩ በሚመለከት የሚነሱ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት መስማማታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። ፕሬዝዳንት አበዱል ፈታ አልሲሲ የታለቁ ህዳሴ ግድብ ውሃ የሚሞላበት ሁኔታ "ግብጽን ይጎዳታል" የሚል ስጋት እንዳላቸው ማንሳታቸውንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጨምረው ተናግረዋል። በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በሩሲያ አፍሪካ የትብብር መድረክ አገራዊ ጥቅሟን ያስጠበቀ ዲፕሎማሲ መስራቷን ነው የገለጹት። በመንግስት እየተተገበረ ካለው የመደመር እሳቤ ከሚያካትታቸው ጉዳዮች መካከል የውጭ ግንኙነት ስራ ሲሆን፤ እሳቤው የአገርን ክብር የጠበቀ፣ ዜጋ ተኮርና በትብብር የታቀፈ ዲፕሎማሲን ያበረታታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም