በአንድ ቀን 10 ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ እየተሰራ መሆኑን ብሔራዊ የደም ባንክ ገለጸ

104
ኢዜአ ጥቅምት 15/2012ዓ/ም ዛሬ በመላው ኢትዮጵያ 10 ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ እየተሰራ መሆኑን ብሔራዊ የደም ባንክ አስታወቀ። "ደም እንለግስ ህይወት እናድን" በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ በመላው ኢትዮጵያ ከ10 ሺህ በላይ ዩኒት ደም የመሰብሳብ መርሃ ግብር እየተካሄደ ይገኛል። ዛሬ ጥቅምት 15 ቀን 2012 ዓ.ም ብሔራዊ የደም ባንክ አገልግሎት ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በአገሪቷ ያሉ 43 ቅርጫፎችን በማሳተፍ 10 ሺህ ዩኒት ደም ከደም ለጋሾች የመሰብሰብ ስራ እየተካሄደ መሆኑን የደም ባንኩ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ያረጋል ባንቴ ተናግረዋል። በዓመት እየተሰበሰበ ያለው 223 ሺህ ዩኒት ደም ሲሆን ለአገሪቷ የሚያስፈልገው ግን አንድ ሚሊዮን ዩኒት ደም መሆኑንም ገልጸዋል። ከአንድ ሰው የሚሰበሰበው ደም ለ42 ቀናት ብቻ የሚቆይ ሲሆን አንድ ሰው ደም ለገሰም አልገሰም አንድ የደም ሴል መቆየት የሚችለው ከ3 እስከ 4 ወራት ብቻ በመሆኑ ሰዎች ለወገናቸው ደም መለገስ ይገባቸዋል ብለዋል። ደም የሚለግሱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ቢመጣም አሁን ብዙ ስራዎች የሚቀሩ መሆኑን ጠቅሰው በትምህርት ቤቶች፣ በሚዲያና በሌሎች ዘዴዎች ግንዛቤ የመፍጠር ስራዎችም በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም ጠቁመዋል። ዛሬ ለመሰብሰብ የታቀደው 10 ሺህ ዩኒት ደም መሆኑን ጠቁመው በቀጣይ በስፋት ለመሰብሰብ ይሰራል ያሉት ዳይረክተሩ፤  አሁን በወር ከ18 ሺህ ዩኒት ደም በላይ ያስፈልጋልም ብለዋል። የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ሳህረላ አብዱላሂ በበኩላቸው የደም ለጋሾችን መረጃ ኮምፒውተራይዝድ ለማድርግ የሚያስችል አሰራር ከዛሬ ጀምሮ አገልግሎት ላይ ይውላልም ብለዋል። በዚህም ደም ለጋሾች በየሶስት ወሩ ደም መስጠት የሚያስችላቸውን መረጃ በአጭር መልክት ለመሳወቅ የሚያስችል አሰራር ከቴሌ ጋር በመሆን የተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል። ከዚህም በተጨማሪ የደም ለጋሹ ደም አገልግሎት ላይ ሲውል የምስጋና መልዕክት ይላክለታል ብለዋል። መሰረታዊ የደም ልገሳ ባህል በአገራችን ባለመዳበሩ አብዛኛው ጊዜ የደም እጥረት ይከሰታል፣ የአገሪቷ ዜጎችም ደም በመለገስ ደም የሚፈልጉ ወገኖቻችንን ህይወት መታደግ አለባቸው ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል። ደም በመለገስ ላይ የነበሩ ሰዎች በሰጡት አስተያየትም ህይወት ለማዳን ደም በመስጠታቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል። ሰው ለሌላው ሰው ደም በመስጠትም የዜጎቹን ህይወት ማዳን አለበት ብለዋል። ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል አቶ ዘውድነህ አብዲ እንዳሉት ደም ሲሰጡ የመጀመሪያቸው ሆኖ  ከእሳቸው በሚሰወድ ደም ሌላውን ማዳን በጣም የሚያስደስታቸው መሆኑን ተናግረዋል። በቀጣይም ደም መስጠት እንደሚፈልጉና ደም በመስጠት በደም እጥረት የሚሞቱትን ሰዎች ለማደን ሁሉም ደም መስጠት እንዳለበት ተናግረዋል። ደም መለገስ ለሌሎች ጥቅም ብቻ ሳይሆን የራስንም የደም አይነት ለማወቅና ያሉበትን የጤንነት ደረጃም ለማወቅ ይረዳልም ብለዋል። ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ አያት ኑር በበኩላቸው ለ6ኛ ጊዜ ደም መለገሳቸውን ጠቅሰው በየጊዜው ደም መስጠት በመቻላቸውና በሰጡት ደምም ሰውን ከማዳን በላይ የሚያስደስት አለመኖሩን ገልጸዋል። ቤተሰቦቿም ደም የመለገስ ባህል ያላቸው መሆኑን ጠቁመው "ሁላችንም  ደም የመለገስ ባህል ልናደርግ ይገባልም" ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም