ሰሞኑን በሀዋሳ በተፈጠረው ግጭት የተፈናቀሉ ሰዎችን ወደ ቤታቸው እንዲመልሱ የአገር ሽማግሌዎች ተጠየቁ

63
ሀዋሳ ሰኔ12/2010 ሰሞኑን በሀዋሳ ተፈጥሮ በነበረው ግጭት የተፈናቀሉ ሰዎችን የአገር ሽማግሌዎች ወደ ቤታቸው እንዲመልሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በሀዋሳ ከተማ ከህዝብ ጋር ባደረጉት ውይይት  ህዝቡ ላነሳቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ ነው። "ግጭቱን ማንም ፈጠረ ማን መከሰት ያልነበረበትና ህዝቡን የማይወክል አሳፋሪ ድርጊት" መሆኑን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት። አጀንዳው በሌላ አካል እንደተሰጠ ቢታወቅም "ህዝቡ በዚያ ተነሳስቶ ተሳታፊ መሆን አይኖርበትም" ብለዋል ዶክተር አብይ። "ልጆቻችንን መከልከልና የጥፋቱን መጠን መቀነስ ነበረብን፤ ሌሎች ሲጠቀሙብን መጠቀሚያ  መሆን የለብንም" ሲሉም መክረዋል። ምክንያቶቹ ከተፈጠረው ግጭትና ከወላይታ ህዝብ ጋር ምንም የማይገናኙ  በመሆናቸውም ለግጭት የማይበቁ ናቸው ብለዋል። ጥቃት የደረሰባቸውን በጉያቸው ደብቀው መያዛቸው የሲዳማ ህዝብ የሚደነቅ ስራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። በቀጣይም የተፈናቀሉና በተለያዩ ቦታ የተጠለሉት ሰዎች "የአገር ሽማግሌዎች ዛሬ ነገ ሳይሉ የተቻለውን ሁሉ ሰርተው ወደ ቤታችው መመለስ አለባቸው" ብለዋል። ክልል ከመሆን ጥያቄ ጋር ተያይዞ ህዝቡን  እስከታች ድረስ አወያይቶ በተደራጀ መልኩ ጥያቄውን ለፌዴራል መንግስት ማቅረብ እንደሚገባም አስገንዝበዋል። በመጀመሪያ ጥቅምና ጉዳቱን ባማከለ መልኩም ውይይት ሊደረግ ይገባል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ሌሎች የልማት ጥያቄዎችና መሰል ችግሮች በሌሎች የአገሪቷ ክፍሎችም ያሉ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ስለሆኑ የተለየ የሚያደርጋቸው አለመሆኑን ገልጸው፤ በቀጣይ ትኩረት ተደርጎ ይሰራል ብለዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም