ሳልቫኪርና ማቻር በአዲስ አበባ ይወያያሉ

2211

አዲስ አበባ  ሰኔ 12/2010 የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንቱ ሳልቫኪር ማያሪዲትና የዋነኛው የተቃዋሚ መሪ ዶክተር ሬክ ማቼር በነገው ዕለት አዲስ አበባ እንደሚገቡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሁለቱ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎቹ አዲስ አበባ የሚገቡት ቀደም ሲል ዶክተር አብይ አህመድ አዲስ አበባ ውስጥ እንዲመካከሩ ያደረጉላቸውን ጥሪ ተቀብለው ነው።

ከዚህ ቀደም ምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) የደቡብ ሱዳን ተደራዳሪዎች በአካል ተገናኝተው መነጋጋር እንዳለባቸው ውሳኔ አሳልፏል።

ይህንንም ውሳኔ ተከትሎ የመንግሥታቱ ድርጅትም የጸጥታው ምክር ቤት በደቡብ ሱዳን ላይ ሊጥለው የነበረውን ማዕቀብ ለ 45 ቀናት እንዲዘገይ ማድረጉን ይታወሳል።

በነገው ዕለት በሚካሄደው ስብሰባው የወቅቱ የኢጋድ ሊቀመንበር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ተገኝተው ተደራዳሪዎቹን ያላቸውን ልዩነት ለማጥበብ እንዲችሉ ያስገነዝቧቸዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ አስታውቋል።

ያም ብቻ ሳይሆን ተደራዳሪዎቹ ለሰላም ዕድል በመስጠት የህዝባቸውን ስደት፣ ሞት፣ መፈናቀልና እንግልት ለማስቆም እንዲሰሩም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሳስባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ከነገ በስቲያም የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥት ባለሥልጣን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እንዲሁም በመሪዎች ደረጃ ስብሰባ በአዲስ አበባ ይካሄዳል ተብሏል።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጠጣር ከ2013 ጀምሮ በደቡብ ሱዳን በተቀሰቀሰው የእርስ በእርስ ግጭት ሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን የሚሆኑ የአገሪቷ ዜጎች ለስደት ተዳርገዋል።

ቁጥራቸው ከ50 ሺ እስከ 300 ሺ የሚጠጉ ዜጎች ደግሞ ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።