በሐረር ከተማ የፍሳሽ ማስወገጃ ቦይ ግንባታ ባለመሰራቱ ስጋት ፈጥሮብናል – የከተማዋ ነዋሪዎች

1592

ሀረር ሰኔ 12/2010 በሐረር ከተማ የፍሳሽ ማስወገጃ ቦይ ግንባታ በበቂ ሁኔታ ባለመከናወኑ የጎርፍ አደጋ  ስጋት እንደፈጠረባቸው አንዳንድ ነዋሪዎች አስታወቁ።

በማህበራት የሚከናውኑ የግንባታ ስራዎች መጓተት ለችግሩ መንስዔ መሆኑን የከተማው ማዘጋጃ ቤት የመሰረተ ልማት ግንባታ ማስፋፊያ ፕሮግራም ጽህፈት ቤት ገልጿል።

በከተማው የቀበሌ 09 አካባቢ ነዋሪ አቶ ሙላቱ አበበ እንደገለጹት  በክረምት ወራት አካባቢው በከፍተኛ ጎርፍ እየተጠቃ ለመንገድ ብልሽትና ለቤቶችም መፍረስ ምክንያት እየሆነ ነው።

የጎርፍ መውረጃ ቦይና መንገድ እንዲገነባ እንዲሁም ህብረተሰቡን ያሳተፈ ሌሎች የልማት ስራዎች እንዲከናወኑ ለሚመለከተው አካል በተደጋጋሚ ጥያቄ  ማቅረባቸውን ተናግረዋል።

”ይሁን እንጂ እስካሁን አንዳችም  መፍትሄ የሚሰጠን አካል በማጣታችን አሁንም በስጋት ላይ እንገኛለን” ሲሉም ገልጸዋል።

የቀበሌ 16 ነዋሪ አቶ ሐይሉ ዘለቀ በበኩላቸው  በአካባቢያቸው ምንም ዓይነት የጎርፍ ማስወገጃ  ቦይም ሆነ  መንገድ ባለመገንባቱ ስጋት እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል፡፡

”በተለይ ህጻናትና አቅመ ደካሞች በክረምት ወቅት ሲቸገሩና ሲጎዱ እመለከታለው” ያሉት አቶ ሐይሉ ለችግሩ መፍትሄ እንዲሰጥ ቢያመለክቱም ምላሽ እንዳላገኙ አስታውቀዋል፡፡

መምህር ሉሉ አየለ ደግሞ በአካባቢው የተጀመሩት የውስጥ ለውስጥ የጥርብ ድንጋይ ንጣፍ መንገድ አለመጠናቀቅ በእንቅስቃሴያቸው ላይ ችግር እየፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

”ለጎርፍ መውረጃ የተሰሩት ቦዮችም እስከ መጨረሻው ባለመዝለቃቸው ዝናብ በዘነበ ቁጥር ጎርፍ  በየቤቱ እየገባ ተቸግረናል” ብለዋል።

በከተማው ማዘጋጃ ቤት የመሰረተ ልማት ግንባታ ማስፋፊያ ፕሮግራም ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብዱልሐፊዝ አህመድ ነዋሪዎች ያነሱት ችግር መንስኤው  ግንባታውን የሚያከናውኑት ማህበራት ስራውን በማጓተታቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ”ስራውን ከሚያከናውኑ ማህበራት ጋር ውል የመሰረዝና በህግ የመጠየቅ ስራ እየተከናወነ ነው” ብለዋል።

የክልሉ መንገዶች ባለስልጣን ስራ አስኪያጅ አቶ መሐመድ ሐሰን በበኩላቸው ህብረተሰቡ ላነሳው ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ኮሚቴ ተዋቅሮ እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

ህብረተሰቡ በዘፈቀደ የሚጥለው ቆሻሻ ቦዩን በመድፈን የጎርፍ አደጋ እንዲፈጠር እያደረገ በመሆኑ ህብረተሰቡ ከዚህ ድርጊት በመቆጠብ ራሱን ከአደጋ መጠበቅ እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡