ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ የኖቤል የሰላም ሽልማት የቱሪዝም እንቅስቃሴውን ያነቃቃዋል

43
ዲላ ጥቅምት 11 /2012  ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድ የኖቤል የሰላም ሽልማት ማሸነፋቸው የቱሪዝም እንቅስቃሴውን እንደሚያነቃቃው የደቡብ ክልል የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ገለጹ፡፡ ባለድርሻዎቹ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት እንዳመለከቱት ሽልማቱ የፈጠረውን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ዘርፉ የሚያመነጨውን ሃብት ለማሳደግ ያስችላል፡፡ አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ የቱሪዝም ግብይት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ኢያሱ ሰለሞን እንደተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ የሽልማቱ ባለቤት መሆናቸው የኢንዱስትሪውን እንቅስቃሴ ያሻሽለዋል። ይህም በክልሉም ሆነ በአገሪቱ የተቀዛቀዘውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ለማሳደግ መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥር እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡ በክልሉ ያለውን እምቅ የቱሪዝም ሃብት ወደ ገንዘብ መለወጥ ካስፈለገ ሕዝቡን የሰላም ባለቤት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ባለሙያው አመልክተዋል፡፡ የጌዴኦ ዞን ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ የቱሪዝምና መስህብ ልማትና ግብይት ዋና የስራ ሂደት አስተባባሪ ወይዘሮ አዜብ በቀለ በበኩላቸው ዶክተር ዓቢይ የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ መሆናቸው የውጭ የቱሪስት ፍሰትን በመጨመር አስተዋጽኦው ጉልህ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አጋጣሚውን በመጠቀምም የሚመጡትን ቱሪስቶች በአገልግሎት አሰጣጥ በማርካት ባለፈ በጎ ስሜት ይዘው እንዲመለሱ ለማድረግ መስራትን ይጠይቃል ብለዋል፡፡ ዞኑ በቀጣዮቹ ሦስት ወራት በርካታ የውጭና የአገር ወስጥ ጎብኚዎች የሚጎበኝበት በመሆኑ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ድጋፍ እየተሰጣቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የአገር በቀል እውቀት ተመራማሪው አቶ ወንድምዓገኝ ኃይሌእንደተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ሽልማቱን ማሸነፋቸው አገር በቀል እውቀትን ለማበልጸግና ለማስተዋወቅ ያስችላል እምነት አላቸው። ጠቅላይ ሚኒስተር በዓለም ታላቁን ሽልማት ማሸነፋቸው የታወጀው መስከረም 30 ቀን 2011 መሆኑ ይታወሳል።              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም