የቅማንት ህዝብ ጥያቄ የተሟላ ህገ-መንግስታዊ ምላሽ አግኝቷል- በቅማንት ብሔረሰብ አስተዳደር የብአዴን ጽሕፈት ቤት

101
ጎንደር ሰኔ 12/2010 የቅማንት ህዝብ የማንነትና የራስ አስተዳደር ጥያቄ በኢትዮጵያ ህገ-መንግስት መሰረት የተሟላ ምላሽ ማግኘቱን በቅማንት ብሔረሰብ አስተዳደር የብአዴን ጽሕፈት ቤት አስታወቀ። የአማራ ክልል ምክር ቤት በቅርቡ ባሳለፈው ውሳኔ መሰረትም የቅማንት ብሄረሰብን የራስ አስተዳደር በቀጣዩ አመት ለመመስረት ዝግጅት ተደርጓል። በቅማንት የብሄረሰብ አስተዳደር የብአዴን ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አበራ አለማየሁ ትናንት ማምሻውን በጎንደር ከተማ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት አስተዳደሩን በይፋ መመስረት እንዲቻል በየደረጃው ዝግጅት በመደረግ ላይ ነው። የክልሉ ምክር ቤት በ42 ቀበሌዎችና በልዩ ወረዳ ደረጃ የብሄረሰብ አስተዳደሩ ይዋቀር የሚለውን ውሳኔ በማሻሻል በ69 ቀበሌና በልዩ የብሄረሰብ ዞን ደረጃ እንዲዋቀር ውሳኔ ማሳለፉን ተናግረዋል። አስተዳደሩን በማዋቀር ረገድ ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንዲቻልም ፖለቲካዊ መዋቅር በመዘርጋት የቅማንት ብሄረሰብ የብአዴን ጽህፈት ቤት መቋቋሙንም ገልጸዋል። "የህዝቡን የዘመናት ጥያቄ እውን ከማድረግ አኳያም የራስ አስተዳደር መዋቅሩን በቀጣዩ አመት ተግባራዊ ማድረግ እንዲቻል የቅማንት ብሄረሰብ አስተዳደር ምክር ቤትን የማቋቋም ስራ ቅድሚያ ይሰጠዋል" ብለዋል። የብሄረሰብ አስተዳደሩ በአፋጣኝ አለመቋቋም የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ፈጥኖ ለመመለስ አለማስቻሉንም ጠቁመዋል። በቀጣዩ አመት አስተዳደሩን በማቋቋምና መንግስታዊ መዋቅሮችን በመዘርጋት ወደ ተሟላ የህዝብ አስተዳደርና የልማት አገልግሎት እንደሚገባም ተናግረዋል። በመተማ አካባቢ የሚገኙ ሶስት ቀበሌዎች ወደ ቅማንት አስተዳደር ካልተካለሉ አስተዳደሩ መመስረት የለበትም በሚል አንዳንድ ወገኖች የያዙት አቋም ትክክለኛ እንዳልሆነም ገልፀዋል። "ጥያቄዎችን በውይይትና በመግባባት መፍታት ይቻላል ያሉት አቶ አለማየሁ የቅማንት ህዝብን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ፈጥኖ ምላሽ በመስጠት በኩል የራስ አስተዳደሩ መዋቀር ወሳኝ ነው" ብለዋል። አዲሱ የቅማንት ብሄረሰብ የአስተዳደር ዞን 69 ቀበሌዎች 3 የገጠር ወረዳዎችና አንድ የከተማ አስተዳደርን አካቶ በመያዝ እንደሚዋቀር በመግለጫው ተመልክቷል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም