ፈተና ሰርተው ለተማሪዎች ሊያቀብሉ የሞከሩ መምህራን በቁጥጥር ስር ዋሉ

3533

አዳማ ሰኔ 122010 በምስራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ ትናንት በተሰጠው የ8ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ሁለት የትምህርት ዓይነቶችን ሰርተው መልሱን ለተማሪዎች ለማቀበል በዝግጅት ላይ የነበሩ ሶስት መምህራን በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የዞኑ ፖሊስ ገለፀ ።

የዞኑ ፖሊስ የህዝብ ግኑኝነት ኃላፊ ኮማንደር አስቻለው ዓለሙ እንደገለፁት መምህራኑ በቁጥጥር ስር የዋሉት የ8ኛ ክፍል የባዮሎጂና የሒሳብ ፈተና ሰርተው መልሱን ለተማሪዎች ለማቀበል በዝግጅት ላይ እንዳሉ ከህብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ ነው ።

ሁለቱ መምህራን ከውጭ ሆነው ፈተናውን ሰርተው የሚያስተላልፉ ሲሆኑ ሶስተኛው  ደግሞ ፈታኝ ሆኖ የተመደበና መልሱን ለተማሪዎች በማቀበል ተግባር የተሰማራ ነው ተብሏል።

ግለሰቦቹ በቁጥጥር ስር ሲውሉ ሰርተው ያዘጋጁት የሁለቱ የትምህርት ዓይነት የፈተና መልስ በእጃቸው መገኘቱን ኮማንደሩ ተናግረዋል።

በቁጥጥር ስር የዋሉት መምህራን ጉዳያቸው እየተጣራ መሆኑንም ከኮማንደር አስቻለው ዓለሙ ገለፃ ለማወቅ ተችሏል።

ፈተና የሚሰጠው የተማሪዎችን እውቀት ለመመዘን በመሆኑ የማይመጥናቸው ውጤት እንዲያገኙ መርዳት ኩረጃን የሚያበረታታና ዜጎችን በራሳቸው እንዳይተማመኑ የሚጎዳ በመሆኑ ህብረተሰቡ በፅናት እንዲከላከለው ኮማንደሩ አሳስበዋል።

ተፈታኝ ተማሪዎችም ኩረጃን በመፀየፍና የፈተና ስርቆትን በማጋለጥ የበኩላቸው እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።