ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሙያዊ ሥነ-ምግባር የማይከተሉ መገናኛ ብዙሃንን አስጠነቀቁ

105
አዲስ አበባ  ጥቅምት 11/2012  ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ሙያዊ ሥነ-ምግባርን ተከትለው የማይሠሩ መገናኛ ብዙሃንን አስጠነቀቁ። አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን የዘር፣ የሃይማኖትና የገንዘብ ነጋዴዎች መቀለጃ እየሆኑ ነው ሲሉ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት። ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ከሰሞኑ የመንግሥትን የትኩረት አቅጣጫዎችን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ማቅረባቸው ይታወሳል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህን ተከትሎ በዛሬው ዕለት ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል። መገናኛ ብዙሃንን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ማብራሪያም ባለፉት ዓመታት መገናኛ ብዙሃን ነጻ የመሆን ፍላጎት ነበራቸው ነፃ ለመሆንም ጥያቄ አቅርበው ነበር ብለዋል። ይሁንና አብዛኛዎቹ መገናኛ ብዙሃን ነፃ ለመሆን ባቀረቡት ጥያቄ ልክ ነፃ ሆነው እየሠሩ አለመሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል። ለኢትዮጵያ ሠላምና ዴሞክራሲ ከመስራት ይልቅ የዘር፣ የሃይማኖት እና የገንዘብ ነጋዴዎች በመሆን እየቀለዱና የሆነ አካልን ወክያለሁ ብለው በሚነግዱ ሰዎች እጅ መውደቃቸውን ተናግረዋል። "ለነዚህ ነጋዴዎች ሕዝቡ ዓይንና ጆሮ ባለመስጠት ሊቀጣቸው ይገባል" ሲሉም መክረዋል። የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣንም ሕጉን መሠረት በማድረግ እርምጃ ሊወስድ እንደሚገባ አሳስበዋል። በተለይም "የውጭ አገር ዜጋ የሆናችሁና የኢትዮጵያ ፓስፖርት የሌላችሁ የሚዲያ ባለቤቶች፤ አገር ሰላም ሲሆንና ስትፈልጉ ያሻችሁን ሠርታችሁ እኛ ስንበጣበጥና ችግር ውስጥ ስንገባ ጥላችሁ የምትሄዱበት አገር ያላችሁ ትዕግስት እያደረግን ያለነው አውዱን ለማስፋት ነው" ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ። "በኢትዮጵያ ሰላምና ህልውና ከመጣ አማርኛም ሆነ ኦሮሚኛ ብትናገሩ እርምጃ እንደምንወስድ ልትገነዘቡ ይገባል" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እኛ የምንሄድበት አገር የለንም አገራችን ይህቺ ብቻ ስለሆነች ሰላም እንፈልጋለን" ብለዋል። በነፃነትና በዴሞክራሲ ስም መቀለድ እንደማይገባ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንዳንድ መገናኛ ብዙሃን እየታየ ያለው ችግር ከሕዝብ ጋር በመሆን በሕግ እልባት እንደሚያገኝ አሳውቀዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም