ቀጣዩ ምርጫ ተአማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የሁሉም አካላት ትብብር ተጠየቀ

289

ኢዜአ፤ ጥቅምት 11/2012 ዓም ቀጣዩ ምርጫ ተአማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የሁሉም አካላትን ትብብር እንደሚጠይቅ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።

ቦርዱ መገናኛ ብዙሃን ለምርጫው ስኬታማነት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቋል።
ከዚህ በፊት የነበሩትን የቦርዱን ተግዳሮቶች በማስወገድ በዚህ ዓመት የሚካሄደውን ምርጫ ተማኒ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።

የቦርዱ የሕዝብ ግንኙነት አማካሪ ወይዘሪት ሶልያና ሽመልስ ዛሬ ለንባብ ከበቃው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ እንዳሉት፤ ከዚህ በፊት ቦርዱ ያከናወናቸው የምርጫ ሂደቶች በርካታ ተግዳሮቶች ነበሩበት።

ቦርዱ የአቅምና የማስፈጸም ብቃት፣ የተአማኒነት፣ የገለልተኝነትና ምህዳሩን የማስፋት ችግሮች በስፋት የሚነሱበት ቅሬታዎች እንደነበሩ አስረድተዋል።

በመሆኑም የሚነሱበትን ችግር ለማስተካከል አዲሱ ቦርድ የራሱን ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ችግሩ በምርጫ ቦርዱ ጥረት ብቻ የሚሳካ ባለመሆኑ ሁሉም አካላት ርብርብ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አማካሪዋ አሳስበዋል።

ምርጫውን በገለልተኝነት ለማስፈጸምና ካለፉት የተሻለ እንዲሆን እየሰራ መሆኑን ገልጸው ያለፈውን ምርጫ ግድፈት ለማረም ቦርዱ ብቸኛ ቁልፍ ባለመሆኑ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎችም በተቀየረው ድባብ እነርሱም ተቀይረው መጓዝ ይኖርባቸዋል ይላሉ አማካሪዋ።

መገናኛ ብዙሃንም ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት እንደሚኖርባቸው አሳስበው የምርጫው ተአማኒነት የሚረጋገጠው በሁሉም አካላት ድምር ውጤት መሆኑን አስምረውበታል።

በተያዘው ዓመት የሚካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲካሄድ መንግሥት ቁርጠኛ አቋም እንዳለው ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የመንግስትን የትኩረት አቅጣጫ ለምክር ቤት አባላት ሲያቀርቡ መናገራቸው ይታወሳል።