ሦስተኛው አገራዊ የመንገድ ደህንነትና የትራንስፖርቴሽን አገልግሎት ቁጥጥር ትግበራ ተጀመረ

69

አዳማ ጥቅምት 11 / 2012 ከተያዘው ወር ጀምሮ ሦስተኛው አገራዊ የመንገድ ደህንነትና የትራንስፖርቴሽን አገልግሎት ቁጥጥር መጀመሩን የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ገለጸ።

ከተያዘው ወር ጀምሮ ሦስተኛው አገራዊ የመንገድ ደህንነትና የትራንስፖርቴሽን አገልግሎት ቁጥጥር መጀመሩን የፌዴራል ትራንስፖርት ባለስልጣን ገለጸ።

በባለስልጣኑ የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ማረጋገጫ ዳይሬክተር አቶ ያዕቆብ በላይ ለኢዜአ እንደገለጹት በቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ ያተኮረ ቁጥጥር እየተተገበረ ነው ።

ቁጥጥሩ በተለይም የደህንነት ቀበቶ መታጠቅ፣የአልኮል ፍተሻ፣የፍጥነት ወሰን መገደቢያና ራዳር ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ አስረድተዋል።

ለዕቅዱ ስኬታማነት በየደረጃው የሚገኙ የክልልና የፌዴራል የትራንስፖርትና የፀጥታ ዘርፍ አካላት የጋራ ዕቅድ አውጥተው ወደ ሥራ መግባታቸውን ተናግረዋል።

በዚህም የሦስተኛ ወገን የመድን ሽፋን ሕግ ትግበራ፣የተሽከርካሪዎች ቴክኒክ ብቃት ፍተሻ፣የቦሎ፣የደህንነት ቀበቶ ማሰርን ጨምሮ 30 የአደጋ መንስዔዎች ተለይተው እየተሰራባቸው መሆኑን አስረድተዋል።

በተያዘው የበጀት ዓመት በሁሉም ተሽከርካሪዎች ላይ የፍጥነት መገደቢያ ቴክኖሎጂ ይገጠማል ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ቴክኖሎጂው በቀዳሚነትም በጭነትና በሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ላይ ይከናወናል ብለዋል።

በሁለተኛ ምዕራፍ ደግሞ በመንግሥት ተቋማት ተሽከርካሪዎችና በቤት መኪናዎች ላይ የፍጥነት መገደቢያ ቴክኖሎጂ እንደሚገጠም አመልክተዋል።

በተጨማሪም የአልኮል መፈተሺያ(ቴስቴር) ቴክኖሎጂ በአዲስ አበባ ከተማ ባስገኘው ውጤት ወደ ክልሎች እንደሚስፋፋ አመልክተዋል።

በዚህም የትራፊክ አደጋን ከ30 እስከ 40 በመቶ ለመቀነስ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

ከቁጥጥር ሥራው ጎን ለጎን የሕዝቡን ግንዛቤ ለማሳደግ ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች ተደራሽ ያደረገ ትምህርታዊ ንቅናቄ ይካሄዳል ብለዋል።

ባለፈው የበጀት ዓመት በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች በተከሰተው የትራፊክ አደጋ ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ የንብረት ውድመት መድረሱን የገለጹት ደግሞ የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ያደታ ናቸው።

አደጋው የመቀነስ አዝማሚያ ቢያሳይም፤ በሕይወትና በንብረት ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት በአሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

ውድመቱ ከአምና ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ200 ሚሊዮን ብር ቅናሽ ማሳየቱንም ገልጸዋል።

ለአደጋው መበራከት መንስዔዎቹ የአሽከርካሪዎች ብቃት ማነስ፣ከተፈቀደው ፍጥነት በላይ ማሽከርከር፣የሥነ ምግባር ጉድለትና ቸልተኝነት፣የተሽከርካሪዎች የቴክኒክ ጉድለቶች የዘርፉ ዋነኛ ችግሮች ናቸው ብለዋልዋል።

የችግሩን አሳሳቢነት ለመግታት በተካሄደው የተቀናጀ አገራዊ ንቅናቄ አደጋው 10 በመቶ መቀነሱን አመልክተዋል።

በበጀት ዓመቱ የሦስተኛ ወገን የመድን ሽፋን ምዝገባ፣የደህንነት ቀበቶ የመታጠቅ ባህል የማዳበርና የማይጠቀሙትን የሙያ ፈቃድ መሰረዝ፣የመንገድ ደህንነት ቁጥጥርና የፍጥነት መገደቢያ ቴክኖሎጂ ተከላ እንደሚከናወንባቸው ዋና ዳይሬክተሩ አመልክተዋል።