ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን ከመገደብ የሚያስቆማት ምንም ነገር የለም - ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ

61
ጥቅምት 11/2012 ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን ከመገደብ የሚያስቆማት ምንም ነገር የለም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመገኘት ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል። ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከምክር ቤት አባላት ግብጽ የግድቡን ግንባታ በተመለከተ ለምታነሳው ጥያቄ የኢትዮጵያ መንግሥት አቋም ምንድን ነው ሲሉ ጠይቀዋቸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩም በምላሻቸው የህዳሴ ግድብ በቀዳሚነት የኢትዮጵያን ክብርና ጥቅም በሚያስከብር መልኩ የሚከናወን ፕሮጀክት መሆኑን አስረድተዋል። ምኞትና ፕሮፓጋንዳ ለይቶ በሳይንስና በእውቀት የሚከወን እንዲሁም የታችኛውን የተፋሰስ አገራት በማይጎዳ መልኩ ይፈጸማል ብለዋል። "ኢትዮጵያ የግብጽንም ሆነ የሱዳንን ሕዝብ የመጉዳት ፍላጎት የላትም፤ ለእኛም ለእነሱም እንዲጠቅም ነው እየገነባነው ያለነው" ብለዋል። በግድቡ ላይ ለሚነሳው የችግሩ መንስዔዎች እኛው ነን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግድቡ ባስቀመጥነው የጊዜ ገደብ ቢጠናቀቅ ኖሮ አሁን አጀንዳው ይሞት ነበር ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በንግግራቸው "እኛ ተኝተንበት ሳንጨርስ ሌሎች በቸገራቸው ቁጥር የሚያነሱትን ኃሳብ የፓርላማ አጀንዳ ማድረግም አያስፈልግም" ብለዋል። አጀንዳ መደረግ ያለበት ሕዝቡ የሚያደርገውን ድጋፍ ማጠናከር አለበት፤ መንግሥትም ድጋፉን በማጠናከር ግደቡ ማለቅ አለበት የሚለው ነው። ለምክር ቤት አባላትም የግድቡን የግንባታ አፈፃፀም በስፍራው በመገኘት ብትጎበኙ የሚል ሀሳብ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅርበዋል። "በእኛና በግብጽ መካከል የተለየ አጀንዳ የሚያነጋግር ነገር የለም፤ ፖለቲካሊ የተስማመንበት ቴክኒካሊም  ባለሙያዎች የሚወያዩበት ነው" ብለዋል። "ከግብጹ ፕሬዳንት ጋር ተወያይተናል፤ ሰሞኑንም ተገናኝተን በጉዳዩ ላይ እንመክርበታለን፤በዚህም ችግር ካለ እንረዳበታለን" ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የኢትዮጵያ ፍላጎት መጠቀም እንጂ ማንንም የመጉዳት ፈላጎት የላትም በማለትም ጠቅሰዋል። እንዲያውም የግብጽ መንግሥትና ሕዝብ የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ልማት መርኃ ግብርን በቀጥታ መደገፍ ያስፈልጋል ብዬ አምናለሁ ብለዋል። "ከተቻለም መጥቶ መትከል፤ አለበለዚያም በሃሳብ መደገፍ ነው፤ ይህም የውኃ ፍሰቱን ዘላቂ ለማድረግ ያግዛል" በማለት ገልጸው፤ ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን ከመገደብ የሚያስቆማት አንዳች ነገር እንደሌለምነው የተናገሩት።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም