መንግሥት ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመከላከል በጥናት ላይ የተመሰረተ እርምጃ ይወስዳል --- ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ

44
ጥቅምት 11/2012 መንግሥት ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመከላከል በጥናት ላይ የተመሰረተ እርምጃ እንደሚወስድ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አስታወቁ። የህዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 5ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመክፈቻ ስነ-ስርዓት ላይ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ያስተላለፉት የመንግስት ዕቅድና ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ዛሬ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ከሰጡባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ሲሆን መንግሥት ዝውውሩን ለመከካከል እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን አንስተዋል። በዚህም እስካሁን በርካታ ቁጥር ያለው ጦር መሳሪያ መያዙን ገልጸዋል። ''ወደ ኢትዮጵያ የሚገባው ጦር መሳሪያ በዋናው መንገድ ብቻም ሳይሆን በግመልና ፈረስ ጭምር የታገዘ ነው'' ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከጎረቤት አገሮች ጋር በመተባበር ጠንካራ ስራ እስካልተከናወነ ድረስ ጦር መሳሪያ ዝውውሩን መግታት ከባድ እንደሚሆንም ገልጸዋል። በመሰረታዊነት ችግሩን ለመፍታት በጥናት የተደገፈ የማስተካከያ እርምጃ እንደሚወሰድ አረጋግጠዋል። ወደአገር የሚገቡት የጦር መሳሪያዎች ብዙም ጥቅም የማይሰጡና ጊዜ ያለፈባቸው መሆናቸውን ጠቅሰው፤ መሳሪያው የሚመጡባቸው አገሮች የቆሻሻ መጣያ ከመሆን መቆጠብ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም