የኑሮ ውድነትን ለመፍታት የተናጠል ሳይሆን የዘላቂነት መፍትሔ ያሻል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ

259
አዲስ አበባ  ጥቅምት 11/2012 የኑሮ ውድነት ለመፍታት መንግስት የተናጠል መፍትሔ ሳይሆን ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችሉ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለጹ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አምስተኛ የስራ ዘመን ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ከምክር ቤቱ አባላት የመንግስትን አቋም አስመልክቶ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል። እየተባባሰ የመጣውን የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ለመፍታት መንግስት ምን እየሰራ ነው? የሚል ጥያቄ ተነስቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በኢትዮጵያ የዋጋ ንረት ጉዳይ በተደጋጋሚ ጊዜ እንደሚነሳና ሰው ሰራሽና መዋቅራዊ ምክንያት እንዳለ ገልጸዋል። መንግስት በአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ችግሮችን መፍታት፣ የማክሮ ኢኮኖሚ ሚዛኑን ማስተካከልና በዘርፉ ባሉ ተቋማት ላይ ማሻሻያ ማድረግ ላይ ያተኮረ ስራ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። በአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያው እይታ ውስጥ የቤትና የምግብ እጥረት፣ ስራ አጥነትና የምናመርተው ምርት በገበያ ከሚፈለገው አንጻር ማነሱ ደግሞ የኑሮ ውድነት እንዲብስ ያደረጉ ምክንያቶች እንደሆኑ ጠቅሰዋል። ለዚህም ችግሮች በተናጥል መፍትሄ መስጠት ያለውን ችግር በዘላቂነት የማይፈታው በመሆኑ በተደራጀ መልኩ ችግሩን ለመፍታት መንግስት እየሰራ ነው ብለዋል። የቤት ችግርን በተመለከተም በአዲስ አበባና ከመዲናዋ ውጪ በሙሉ ኢንቨስትመንትና በሽርክና ሰፋፊ የቤቶች ግንባታ እንዲሳተፉ መንግስት ከባለሀብቶች ጋር እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። ለሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ቤት የሚገነቡ ባለሀብቶች መገኘታቸውንም በማሳያነት ጠቅሰዋል። አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ጎተራ ላይ የለገሀሩን የሚያክል 'አዲስ ቱሞሮ' የሚል ትልቅ ከተማ ለመስራት ከቻይና መንግስት ኩባንያ ጋር ስምምነት እንደሚፈረምም ገልጸዋል። የሚሰራው ከተማ ዲዛይንና ቦታው ተዘጋጅቶ መጠናቀቁንና ፕሮጀክቱ ለዲፕሎማቶችና የተሻለ ቤት ለሚፈልጉ ሰዎች ያለውን የቤት ችግር ይፈታል ተብሎ እንደታመነበትም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት። በተጨማሪም የቤት ችግሩን ለመፍታት ከአራት እስከ አምስት ሺህ የጎዳና ተዳዳሪዎችን የሚያነሳ የቤት ግንባታ እየተከናወነ መሆኑንና የስራ እድል በመፍጠርም ዘላቂ መፍትሄ ለማበጀት የታሰበ መሆኑን ተናግረዋል። ይህም የጎዳና ተዳዳሪዎች በስራ እንዲሰማሩ በማድረግ የስራ አጥነት ችግር መፍታት እንደሚያስችል በማከል። በምግብ ላይ ተከስቶ የነበረውን የምግብ የዋጋ ንረት ለማረጋጋትም መንግስት ከክልሎች ጋር በመተባበር አቅርቦት የማምጣት ተግባር ማከናወኑንም አውስተዋል። በመዲናዋ እየተገነባ ያለውና በቀን ከአንድ ሚሊዮን ዳቦ በላይ የሚያመርተው ፋብሪካ ከሁለት ወራት በኋላ ስራ እንደሚጀምርና ለዜጎች ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ ዳቦ እንዲያገኙ እንደሚደረግ ጠቅሰዋል። በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ድጋፍ አማካኝነት እየተገነባ ያለውና በቀን ከ10 ሚሊዮን ዳቦ በላይ መጋገር የሚያስችለው የዳቦ ፋብሪካም በበጀት ዓመቱ መጨረሻ እንደሚጠናቀቅም ጠቁመዋል። ከቤትና ከዳቦ በተጨማሪም የከተማ ግብርናን የማስፋፋት ስራ እንዲስፋፋ በማድረግ የዋጋ ማረጋጋት ስራ እንደሚከናወንም ጠቁመዋል። ዘንድሮ ከፍተኛ ዝናብ መገኘቱንና የተገኘው ዝናብ በዝናባማ አካባቢዎች ብቻ ሳይሆን ሌሎች ዝናብ በማይጥልባቸው ቦታዎችም ዝናብ እንደነበረ አስታውሰዋል። ከጣለው ዝናብ አንጻርም አሁን ይሄ ነው ባይባልም በተያዘው ዓመት ከፍተኛ ምርት እንደሚጠበቅ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስረዱት። በበጀት ዓመቱ ሩብ ዓመት የግብርና ኤክስፖርት አፈጻጸም 101 በመቶ እንደነበረና ይህም ምርታማነትን ከማሳደግ አኳያ መልካም የሆነ ነገር እንደሆነ አንስተዋል። በተቀናጀ መልኩ የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ሲሳለጥ የኑሮ ውድነቱ ጉዳይ መስምር እንደሚይዝም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል። የኑሮ ውድነት በአጭር ጊዜ የማይፈታ እንዳልሆነና ዘላቂ ስራ እንደሚያስፈልግም አክለዋል። አቅም በፈቀደ መልኩ የኑሮ ውድነትን ለመፍታት ጥረት እንደሚደረግና የተናጥል መፍትሔ ሳይሆን ዘላቂነት ያለው የማሻሻያ ስራዎች እንደሚሰራም አመልክተዋል። ኢኮኖሚውን ከፍ በማድረግም የኑሮ ውድነት መቀነስና የኢትዮጵያን ብልጽግና ጉዞ የማፋጠን ስራ በሚል የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው የመጀመሪያውን መሰረት ዘንድሮ መጣል አለበት ተብሎ እየተሰራ እንደሚገኝም አክለዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም