ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ሩሲያ አቀኑ

182
ጥቅምት 11/2012 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ዛሬ ወደ ሩሲያ አቅንተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሩሲያ ያቀኑት በመጀመሪያው የሩሲያ-አፍሪካ የኢኮኖሚ ፎረም ለመሳተፍ ነው። ፎረሙ እንደ አውሮጳዊያኑ አቆጣጠር ከጥቅምት 23-24 ለሁለት ቀናት በሩሲያዋ ሶቺ ከተማ ይካሄዳል። በሩሲያና በአፍሪካ መካካል ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ግንኙነትን ማጠናከር የፎረሙ ዋነኛ ዓላማ እንደሆነ ተገልጿል። ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በተጨማሪ የ46 የአፍሪካ አገራት መሪዎች፣ በአህጉሪቱ የሚገኝ የንግድ ማኅበረሰብና ሌሎች ዓለም አቀፋዊ ተቋማት በፎረሙ እንደሚሳተፉ ይጠበቃል። ፎረሙን የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና የወቅቱ የአፍሪካ ኀብረት ሊቀ መንበር የግብፁ ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታ አልሲሲ እንደሚከፍቱት መረጃዎች ጠቁመዋል። ሩሲያ በቀድሞው ሶቬት ኅብረት ጥላ ስር በአፍሪካ የነበራት ተጽዕኖ ከፍተኛ ሲሆን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቃት በኋላ ግንኙነቱ ቀስ በቀስ እየቀነሰ መሄዱ ይነገራል። አገሪቷ እንደ አውሮጳዊያን አቆጣጠር በ2018 ከሰሃራ በታች ካሉ አገራት ጋር ያደረገችው የንግድ ልውውጥ 20 ቢሊዮን ዶላር ብቻ መሆኑ ለአብነት ይጠቀሳል። በአንጻሩ የአውሮፓ ኅብረት አገራትና ቻይና በቅደም ተከተል የ300 እና የ200 ቢሊዮን ዶላር የንግድ ልውውጥ ከአህጉረ አፍሪካ ጋር አድርገዋል። ፎረሙ ሩሲያ በአፍሪካ ያለውን ምቹ የቢዝነስ ሁኔታ በመጠቀም ረገድ ያለባትን ክፍተት ለመቅረፍ ቁርጠኛ አቋም መያዟን እንደሚያሳይም የምጣኔ ሃብት ምሁራን እየተነተኑ ነው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም