አርሶ አደሩ ዘመናዊ አመራረትን በመከተል ራሱን ብሎም ሀገሪቱን  ሊጠቅም ይገባል- የኦሮሚያ ምክትል ፕሬዘዳንት

87
መቱ ኢዜአ ጥቅምት 10/2012 አርሶ አደሩ ዘመናዊ አመራረትን በመከተል ራሱን ብሎም ሀገሪቱን  ሊጠቅም ይገባል ሲሉ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ምክትል ፕሬዘዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ተናገሩ። ፕሬዘዳንቱ ከኢሉአባቦር ዞን ከተወጣጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በልማት ዙሪያ ዛሬ በመቱ ከተማ ተወያይተዋል። ተሳታፊዎቹ በውይይቱ ወቅት የመንገድ ፣የግብርና ምርቶች ገበያና ሌላም የልማት ችግሮችን አንሰተው እንዲፈታላቸው ጠይቀዋል። ምክትል ፕሬዚደንቱ እንዳሉት አካባቢው በተፈጥሮ ደን የበለፀገ ፣ ለቡና እና ማር ምርት አመቺ በመሆኑ አርሶ አደሩ ዘመናዊ አመራረትን በመከተል ራሱን ብሎም ሀገሪቱን  ሊጠቅም ይገባል:: የክልሉ መንግስት ለገጠር ሜካናይዜሽን ፣ለመሰረተ ልማት ማስፋፋትና የስራ ዕድል ፈጠራ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል:: እንደ አቶ ሽመልስ ገለጻ በክልሉ ዞኖችና ወረዳዎች  የመንገድ መሰረተ ልማት ችግሮች በመለየት ለመፍታት መንግስት ጥረት እያደረገ ነው። በቡና ልማት የተሰማሩ አርሶ አደሮች ምርትን በብዛት እና በጥራት በማምረት ቀጥታ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የክልሉ መንግስት የሙያ የቴክኖሎጂና ሌሎች ድጋፎች እንደሚያደርግም አስረድተዋል። መንግስት ለህዝብ ጥያቄ ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ደረጃ በደረጃ ለመመለስ በትኩረት እየሰራ መሆኑን አመልክተው ህብረተሰቡም ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። ምክትል ፕሬዚደንቱ በኢሉአባቦር ዞን የነበራቸው ቆይታ አጠናቀው ወደ ጅማ ዞን አምርተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም