''እኔ አውቅልሃለሁ አስተሳሰብ'' ተሰሚነታችንን ሸርሽሯል - የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች

75

አዲስ አበባ ጥቅምት 10/2012 "የእኛ ሚናችንን በተገቢው አለመወጣትና በወጣቱ ዘንድ ያለው እኔ አውቅልሃለሁ አስተሳሰብ ተሰሚነታችንን ሸርሽሯል'' ሲሉ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ገለጹ።

በኢትዮጵያ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች በሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ ከፍተኛ ተሰሚነትና ተቀባይነት አላቸው።

የሃይማኖት አባት ወይም የአገር ሽማግሌ 'ተው' ብሎ የማይተው 'አድርግ' ብሎ የማያደርግ ሰው በህብረተሰቡ ዘንድ የሚደርስበት መገለልም ቀላል አልነበረም።

ይሁንና  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች በተለይም በወጣቱ ዘንድ የነበራቸው ተሰሚነት እየተሸረሸረ መምጣቱን አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ አባቶች ተናግረዋል።

የአገር ሽማግሌው ከስልጤ ዞን ሀጂ መሃመድ ተሊል  ''ወጣቱ እምነት በሽማግሌዎችና በሃይማኖት አባቶች እምነት ያጣበት መጤ አስተሳሰብ አለ፤ ይሄ የኛም ችግር ነው። የእነሱ ብቻ ችግር አይደለም፤ እኛም ወደ ካድሬነት ተለውጠን በየስብሰባው እንደዚህ በሚዲያ እየቀዳችሁን እያስተላለፋችሁን እያየ ይሄ የመንግስት ካድሬ ነው እያለ ላይሰማን ችሏል።''ብለዋል

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መልዓከ አርያም ቀሲስ አስረስ በበኩላቸው ''አሁን የመጣብን ጊዜ ወጣቱ የሃይማኖት አባቶችን፣ ሽማግሌዎችን ያለመስማት፤ ስሜታዊ መሆን፤ ጥላቻ ነው እየታየበት ያለው።''

በኢፌዴሪ ህገ መንግስት ሃይማኖትና መንግስት የተለያዩ መሆናቸውን በግልጽ ይደነግጋል። መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም ሃይማኖትም በመንግስት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም።

ይሁንና መንግስትም ሆነ አንዳንድ አባቶች ይህን ህገ-መንግስታዊ ድንጋጌ ሲሽሩ ይስተዋላል።

ይህም ህዝቡ በአባቶች ላይ እምነት እንዲያጣ ካደረጉ ምክንያቶች አንዱ መሆኑን አስተያየት ሰጪዎቹ አክለዋል።

የቀደመውን ተሰሚነት ለመመለስና የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎችም የተሰጣቸውን ሃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ ምን ሊደረግ ይገባል? ለሚለውም ምላሽ አላቸው።

በደቡብ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼህ አብዱልከሪም በድረዲን በበኩላቸው ''አንዳንዴ የሃይማኖት አባቶችም ወደ ፖለቲካው ጠጋ ይሉና ነገሮችን ያበላሻሉ።

የአገር ሽማግሌዎችን በተመሳሳይ ከዚህ ወጣ ብለን እኛ የራሳችን የሆነ አካሄድ አለን የአገር ሽማግሌዎችም በተመሳሳይ መንግስትን የምንፈልገው ጉዳይ አለ፤ ግን ሁሉ ነገራችንን መንግስት ላይ ስራ ማብዛት የለብንም የሃይማኖት አባት የሃይማኖት አባት ስራ መስራት ነው ያለበት፤ የአገር ሽማግሌ የአገር ሽማግሌ ስራ መስራት ነው ያለበት።''

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም