የወጪ ምርቶች ውል አስተዳደር መመሪያ ተግባራዊ ሊሆን ነው

144
ጥቅምት 10/2012 ንግድ ሚኒስቴር የወጪ ምርቶች ውል ምዝገባና አፈጻጸም መመሪያን በቀጣይ ሳምንት ተግባራዊ ሊያደርግ ነው። መመሪያው  የወጪ ምርቶችን ወደ ውጭ አገር ለመላክ በሚፈጸሙ በማንኛውም ውሎችና ምርት ላኪዎች ላይ ተፈጻሚ የሚሆን ነው። የወጪ ምርቶችን ወደ ውጭ ለመላክ የሚገቡ ውሎችን መመዝገብ፤ የላኪዎችን ተግባር፣ ሃላፊነትና ግዴታን ጨምሮ አምስት ክፍሎች ያሉት ይህ መመሪያ ከጥቅምት 17 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋልም ተብሏል። የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ መመሪያውን አስመልክተው ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ እስካሁን ባለው አሰራር በወጭ ንግድ ላይ የተሰማሩ ላኪዎችን ከውል አፈጻጸም ጋር በተገናኘ ቁጥጥርና ክትትል ማድረግ የሚያስችል አሰራር እንዳልነበረ ገልጸዋል። አክለውም የጥራት፣ ኮንትራት ውል ማምረትና ሌሎች ችግሮች ሲያጋጥሙ መቆጣጠር የሚያስችል ስርአት ባለመዘርጋቱም ላኪዎች በራሳቸው መንገድ ሲመሩ ነበር ብለዋል። ችግሩ በአለም አቀፍ ገበያ የኢትዮጵያ ነጋዴዎችን ተአማኒነት የሚያሳጣ፣ በሂደትም የአገሪቱን ምርት ከአለም አቀፍ ገበያ ሊያወጣ የሚችልና የአገር ገጽታን እያበላሸ የሚሄድ መሆኑንም አንስተዋል። የዋጋ ቁጥጥር ስርአት ባለመኖሩም "አንዱ ላኪ ኮንትራት ከጨረሰ በኋላ ሌላኛው ላኪ እኔ ባነሰ ዋጋ አቀርብልሃለሁ ከዚያኛው ላኪ አትግዛ" በማለት በላኪዎች መካካል ጤናማ የውድድር ስርአት እንዳልነበረ አንስተዋል። ከአለም አቀፍ ዋጋ በታች አሳንሶ መላክ ከወጪ ንግዱ ዋነኛ መገለጫዎች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ይህም የአገሪቷን "የወጭ ንግድ በማዛባት አሉታዊ ተጽእኖ ፈጥሯል" ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታው በማብራሪያቸው። ውሉን ካለማክበር ጋር በተገናኘም የኢትዮጵያን ምርት ከሚቀበሉ አገራት ቀብድ በመውሰድ ምርቱን ሳያቀርቡ የሚጠፉ ላኪዎች መኖራቸውን ከደንበኞች በተደጋጋሚ ቅሬታዎች ይቀርቡ እንደነበር ተናግረዋል። እነዚህንና ሌሎች በወጪ ንግድ ላይ ያሉ ተያያዥ ችግሮችን ለመፍታት አዲስ የውል አስተዳደር ስርአት መዘርጋት እንዳስፈለገ በማከል። ይህ የውል አስተዳደር ስርአት የወጪ ምርት ላኪዎች የገቡትን ውል ሳይጥሱ ጥራቱን የጠበቀና ተአማኒ የሆነ የንግድ ስርአት ለመገንባት ያስችላቸዋል ብለዋል። መመሪያው ላኪዎች ወደ ውጭ የሚልኩትን ምርት ከዋጋ፣ ጥራትና ውል አፈጻጸም አኳያ በትክክል ስለመፈጸሙ ያረጋግጣል ብለዋል። ቀደም ሲል ከኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከፍ ባለ ዋጋ በመግዛት ለብሔራዊ ባንክ ያነሳ ዋጋ ያስመዘግቡ የነበሩ ላኪዎችን መቆጣጠር በሚያስችል ሁኔታ የተዘጋጀ እንደሆነም ነው የተናገሩት። እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ በምርት ገበያ የገቡ ምርቶችን ሃሰተኛ ኪሳራ እያስመዘገቡ ያሉ ላኪዎች ላይም ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ የውጭ ንግድ አትራፊ ቢዝነስ እንዲሆን ያደርጋል ብለዋል። አሰራሩ በውድድር ላይ የተመሰረተ የንግድ ስርአትን ለማረጋገጥ ያግዛል የተባለ ሲሆን በመነሻነት ነጭ ቦለቄን፣ ማሾን፣ አኩሪ አተርንና ሌሎች ወደ ኢትዮጵያ ምርት ገበያ የገቡ ምርቶች ላይ በአስገዳጅ ሁኔታ ተፈጻሚ እንደሚሆንም ተናግረዋል። በአሰራሩ መሰረት ላኪዎች ከደንበኞቻቸው ጋር በገቡት ውል መሰረት ምርቱን ማቅረብ የሚችሉበት እድል ተሰጥቷቸው ማቅረብ ካልቻሉ ፈቃድ እስከማገድ የሚደርስ ህጋዊ እርምጃዎች እንደሚወሰድባቸውም ተናግረዋል። ህግና ስርአትን አክብረው የሚሰሩ ላኪዎችን ከኪሳራ ማውጣት፣ የወጪ ንግድን ማጠናከር፣ የተበላሹ ውሎች እንዳይመዘገቡ ማድረግ፣ በውድድር ላይ የተመሰረተ የወጪ ንግድ መገንባት ደግሞ ከዋነኛ ዓላማዎቹ ናቸው። መመሪያው የንግዱ ማህበረሰብ፣ ብሔራዊ ባንክ፣ ቡናና ሻይ ባለስልጣን፣ የኢትዮያ ምርት ገበያንና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ የተዘጋጀ ሲሆን በ2011 ዓ.ም ውይይት ተደርጎበታልም ተብሏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም