በኬኒያ በደረሰ የጎርፍ አደጋ የ20 ሰዎች ህይወት አለፈ

138

ኢዜአ፤ ጥቅምት 10/2012 ኬኒያ ውስጥ ሰሞኑን የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ የ20 ሰዎች ህይወት ማለፉን የሀገሪቱ ቀይ መስቀል ማህበር ገለፀ።

የኬኒያ ሰብአዊ መብት ድርጅት በበኩሉ እስካሁን ድረስ በአደጋው ምክንያት በማራካዊት፣ ኪቱይ፣ ሜሩ፣ ቱርካና እና ዋጅር በተባሉ  አውራጃዎች 18 ሰዎች መሞታቸውን  አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡

በቀጣይም በሰሜን ምስራቅ፣ በምስራቅና ምዕራብ ስምጥ ሸለቆዎች፣ በደቡብ ምስራቅ ዝቅተኛ ቦታዎች እንዲሁም በባህር ዳርቻዎች አካባቢ ዝናቡ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚችል የኬኒያ  የሜትሮሎጂ መስሪያ ቤት ስጋቱን አስቀምጧል።

የአየር ትንባያ መረጃውን ተከትሎም ወቅቱ አስቸጋሪ በመሆኑ ኬኒያውያን ከቤታቸው  በሚወጡበት ወቅት ጃንጥላ መያዝን እንዳይረሱ፣ ከጎርፍ አደጋ ራሳቸውን እንዲጠብቁ፣ ዝናብ በሚጥልበት ወቅት ከፍ ወዳለ ቦታ እንዲወጡና እንዳያሽከረክሩ እንዲሁም ጎርፍ በሚስተዋልባቸው አካባቢዎች ዋና እንዳይዋኙ ሲሉ የቀይ መስቀል ማህበር የኮሙኒኬሽን ማናጀር ፒተር አብዋ መልክታቸውን አስተላልፈዋል።

ማህበሩ አደጋው በተከሰተባቸው ዋጅር በተባለ አካባቢ 8 ሺህ የቤተሰብ አባላት አና ማንደራ አካባቢ  የአደጋው ሰለባ ለሆኑ 5 ሺህ  የቤተሰብ አባለት ጊዜያዊ መጠለያ ካምፕ ለመስራት በዝግጅት ላይ መሆኑን  ገልጿል።

ከዚህ ቀደም በምስራቅ አፍሪካ አገራት ዙሪያ ከ 20 ሺህ በሚበልጡ አባወራዎች ላይ የጎርፍ መጥለቅለቅ ደርሶባቸው የነበረ ሲሆን በተደረገ ርብርብ ግን ከአደጋ መታደግ መቻሉን ቢቢሲ ዘግቧል።