የመደመር እሳቤ ለሀገር በቀል ችግር ሀገር በቀል መፍትሄ የሚሰጥ ነው- የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች

175

ደብረ ብርሃን/ ባሌ/አርበባምንጭ/ ዲላ/ ነቀምት ጥቅምት 9 /2012 /  የመደመር እሳቤ ለሀገር በቀል ችግር አገር በቀል መፍትሄ የሚሰጥ መሆኑ የገለፀ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ የተጻፈው “መደመር” የተሰኘው መጽሀፍ በሮቤ፣ አርባምንጭ፣ ዲላ፣ነቀምትና ደብረብርሀን ከተሞች ትላንት ተመርቋል።

በደብረ ብርሀን በተካሄደው የምረቃ ስነ ስርአት የተገኙት የዉጪ ጉዳይ ሚስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው እንደገለፁት የመደመር እሳቤ ሀገር በቀል እውቀትን በመጠቀም የኢትዮጰያን መጻእይ እጣ ፈንታ በጎ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል ።

የመደመር አስተሳሰብ ለኢትዮጰያ ዘላቂ ሰላም የሚበጅ እንደሆነም አመላክተዋል ።

የፌደራል ምክትል ጠቅላይ አዓቃቤያን ህግ ዶክተር ጌድዮን ጢሞትዮስ “መደመር የተለያዩ አስተሳሰቦችና አመለካከቶች በአንድነት ለህብረት መቆማቸውንና መደጋገፍን የሚየሳይ ነው” ብለዋል።

በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የፌደራል፣ የክልል፣ የዞንና ከተማ ከፍተኛ አመራሮች፣ምሁራን፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የነዋሪዎች ተወካዮች ተገኝተዋል ።

በሮቤ በተካሄደው የምረቃ ስነ ስርዓት ላይ የተገኙት የኦዲፒ ማዕከላዊ  ኮሚቴ  አባል  አቶ ካሰሁን ጎፌ በበኩላቸው የመደመር እሳቤ የሰውን ልጅ ማንነትና ተፈጥሮን ያገናዘበ ለአገር  በቀል  ችግር  አገር  በቀል  መፍትሄ  መስጠት ይስችላል።

የኦሮሚያ ትራንስፖርት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር ምህረቱ ሻንቆ መጽሀፉ የሰው ልጆችን ማንነትና ፍላጎት መስረት ማድረጉ ልዩ እንደሚያደርገው ተናግረዋል ።

በምረቃ  ስነ ስርዓቱ ላይ ከዞኑ 18 ወረዳዎችና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች የተወከሉ የህብረተሰብ ክፍሎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል ፡፡

በአርባምንጭ በተካሄደው የምረቃ ስነ ስርዓይ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ የኢህአዴግ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ በበኩላቸው “መደመር መጽሐፍ አገራችንን ወደ ለውጥ ጎዳና የሚመራ ፍኖተ ካርታ ነው” ብለዋል ።

“አገራችን በከፍተኛ ለውጥ ውስጥ ብትሆንም በጋራ ልናልፋቸው የሚገቡን በርካታ ተግዳሮቶች አሉ” ያሉት አቶ የስፋዬ ያለንን ሀብት፣ ዕውቀት፣ ክህሎትና ልምድ በማከማቸት ለለውጥ ማዋል እንደሚገባ አመላክተዋል።

በደቡብ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ “የኢትዮጵያ ችግር ሊፈታ የሚችለው ስንደመር ብቻ ነው” ብለዋል፡፡

“መደመራችን ለሰላም፣ ለልማትና ዴሞክራሲ መረጋገጥ ትልቅ መሣሪያ ነው” ሲሉም ተናግረዋል ።

ከጋሞ ሽማግሌዎች መካከል ካዎ ደምሴ ፃራ በበኩላቸው ዶክተር አብይ አህመድ ለኢትዮጵያ አንድነት ከመስበክ አልፈው የመደመር እሳቤ የያዘ መጽሐፍ ማበርከታቸው የሀገሪቱ ከፍታ ዳግም እንዲያንሰራራ የሚያደርገ መሆኑን ተናግረዋል ።

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የጋሞና የጎፋ ዞኖች እንዲሁም የባስከቶ ልዩ ወረዳ አመራሮች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ወጣቶች፣ ሴቶችና ባለሀብቶች ተገኝተዋል፡፡

“መደመር የጭቁን ሕዝቦችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ያጠናክራል” በሚል የተገለፀው ደግሞ በዲላ ከተማ በተካሄደው የምረቃ ስነ ስርዓት ላይ ነው።

መጽሀፉ ምረቃ ስነ ስርዓት ላይ ከጌዴኦ፣ ቡርጅና አማሮ የተወከሉ ህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ተወካኝ አቶ ቢንያም ኤሮ መጽሀፉ ለኢትዮጱያ ፖሊቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ብልጽግና ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል ።

መጽሀፉ ከባሕር ማዶ ትርክት ተላቆ ለሀገራዊ ችግር ሀገራዊ መፍትሔ የሚሰጥ ጽንሰ ሃሳብ የተንጸባረቀበት እንደሆነም አመላክተዋል ።

የመደመር እሳቤ መሰረቱ ሰው መሆኑን ጠቁመው በተለይ ከቁሳዊ ግንባታ በተጓዳኝ የሰዎችን አእምሮ በማበልጸግ ሁለንተናዊ ብለጽግናን ማረጋገጥ መሆኑን አብራርተዋል ።

የደኢሕዴን የከተማ ፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ ወይዘሮ ፋጤ ሰርሜሎ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኖቤል የሰላም ሽልማት ባሸነፉ ማግስት መጽሀፉ መመረቁ ደስታችንን እጥፍ ድርብ አድርጎታል” ብለዋል ።

“የመጽሀፉ እሳቤ የቀደመውን ጥሎ አዲስ የሚያነሳ ሳይሆን ብዝሃነትንና ታሪከን ጠብቆ ለተጨማሪ ስኬት ለመተባበር የሚያነሳሳ ነው” ሲሉም ተናግረዋል ።

የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገዙ አሰፋ ሀገራዊ አንድነት የሚንፀባረቅበት መጽሀፍ በከተማው መመረቁ አስደሳች መሆኑን ገልፀዋል ።

“የመደመር እሳቤ የተበታተነ ሀብት፣ አቅምና ጉልበትን በማሰባሰብ ለላቀ ስኬት ለመነሳሳት ጠቃሚ ነው” ብለዋል ።

በነቀምቴ ከተማ በተካሄደው የምረቃ ስነ ስርዓት ላይ የተገኙት በኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው መዕሀፉ የኢትዮጵያ፣ ብሄር ብሄረሰቦችን አንድነት ለማጠናከር ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

“የመደመር ፍልስፍና ቅድመ አያቶቻችን ያወረሱን የመቻቻል፣ የመፈቃቀር፣ የመዋደድና የአብሮነት ባህሎቻችንን በማዳበር ለቀጣይ ትውልድ እንድናስተላልፍ የሚያግዝ ነው” ብለዋል ።

እንደ አቶ ሽመልስ ገለጻ መጽሀፉ የሀገርቱን  ማህበራዊ፣ አኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች ለመፍታት ሚናው የጎላ ነው።

በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የክልልና ዞን ከፍተኛ አመራሮች፣ የነቀምቴ ከተማ ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል ።