የ አርጆ ጉዳቱ -ጅርማ ሶጌ የጠጠር የመንገድ ግንባታ ተጀመረ

357

ነቀምቴ ኢዜአ ጥቅምት 9 ቀን 2012 ዓም -የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በመደበው 392 ሚሊዮን ብር የአርጆ ጉዳቱ -ጅርማ ሶጌ የጠጠር የመንገድ ግንባታ ዛሬ ተጀመረ።

መንገዱ የኦሮሚያና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎችን በማገኛኘት  ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እንደሚፈታ ተገልጸል ።

በምስራቅ ወለጋ ዞን ድጋ ወረዳ ላሊስቱ ዲምቱ ቀበሌ የመሰረት ድንጋይ በማስቀመጥ የመንገዱን ግንባታ ስራ ያስጀመሩት የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳና የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሐሰን ናቸው።

የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ  በወቅቱ እንደገለፁት መንገዱ በሁለቱ ክልሎች መካከል ግንኙነት በማጠናከር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻቸውን በጋራ ለመፍታት ያስችላል ።

የግንባታው መጀመር  ክልሎቹ በትምህርት፣ በጤና፣ በውሃ፣ በኤሌክትሪክና በሌሎች መሰረተ ልማቶች ትስስር እንዲኖራቸው የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል ።

መንገዱ ክልሎቹ ለተጀመረው ሀገራዊ የመደመር ፍልስፍናን በማሳካት የኢትዮጵያን አንድነት፣ብልጽግናና እድገት በተግባር ለማረጋገጥ አቅም እንደሚሆናቸውም አመላክተዋል ።

“በግልና በተናጠል ከመስራት አብሮነትና አንድነት ውጤታማ  ያደርጋል” ያሉት ደግሞ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሐሰን

የሁለቱ ክልሎች የጋራ የሰላምና የልማት ፕሮጀክት መቀረጹ  ህዝቦችን  በልማት በማተሳሰር በጋራና እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያደርጋቸው መሆኑን ጠቅሰዋል ።

በስነ ስርአቱ ላይ የተገኙት ጋምቤላ ክልል መርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦሞድ ኡጁሉ  በበኩላቸው  በክልሎቹ የተጀመረውን ግንኙነት ለማጠናከር ክልላቸው ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል ።

በኦሮሚያ ክልል በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ የገጠር ዘርፍ ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አማንቴ ” ክልሎቹ በሳራቸው ልማትና ሰላም ዙርያ መወያየትና በጋራ መስራት መጀመራቸው የመደመር እሳቤን  በተግባር ያሳየ ነው” ብለዋል ።

የምስራቅ ወለጋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሳምሶን ብራቱ የመንገዱ መገንባት የትራንስፖርት ችግርን ከመፍታት ባለፈ የክልሎቹን የሀዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንደሚያጠናክር ተናግረዋል ።

ግንባታው የተጀመረው መንገድ 46 ኪሎሜትር ርዝመት ያለውና በሶስት አመት ጊዜ ውስጥ የሚጠናቀቅ መሆኑ ታውቋል ።