የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለሶስት ሺህ አንድ መቶ አዲስ ገቢ ተማሪዎች ደማቅ አቀባበል አደረገ

182

ጥቅምት 9/2012 የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለሶስት ሺህ አንድ መቶ አዲስ ገቢ ተማሪዎች ደማቅ አቀባበል አደረገ።

ተማሪዎቹ ዛሬ በመስቀል አደባባይ በተደረገው 5ኛው ዙር የከተማው የማስ ስፖርት ላይም ተሳትፈዋል።
በአካላዊ እንቅስቃሴ ጤናማ ማህበረሰብ መፍጠርን ያለመ የማስ ስፖርት በከተማ አስተዳደሩ በየወሩ መጨረሻ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

መንገዶችን ከሞተር ነጻ በማድረግ የሚደረገው ይህ የማስ ስፖርት አሁን አሁን በየ አስራ አምስት ቀናት እየተደረገም ይገኛል።

የዛሬውን የአዲስ አበባ የማስ ስፖርት ልዩ የሚያደርገው ታዲያ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተመደቡ አዲስ ገቢ ተማሪዎችን ማሳተፉና ተማሪዎቹን በቀላሉ ከከተማው ነዋሪ ጋር ማስተዋወቁ ነው።

በአቀባበሉና በማስ ስፖርቱ የተሳተፉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝደንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና የማስ ስፖርቱ ተማሪዎቹ ከማህበረሰቡ ጋር እንዲገናኙ ዕድል መፍጠሩን ተናግረዋል።

ከማስ ስፖርቱ በተጨማሪም ተማሪዎቹ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የተመረጡ ቦታዎችን ዛሬ እንደሚጎበኙም ገልጸዋል ፕሬዝደንቱ።

ዩኒቨርሲቲው ለአዲስ ገቢ ተማሪዎች ትምህርት ተኮር እና ማህበራዊ የሆኑ ጉዳዮች ላይ የተለያዩ ስልጠናዎች አዘጋጅቶ ሲሰጣቸው እንደነበረም ተገልጿል።

ባሉት የሙያ ማሰልጠኛ ማዕከላትም ተማሪዎቹ ከትምህርታቸው ውጪ ሙያቸውን የሚያበለፅጉበትና ሌሎች     ክህሎቶች የሚያገኙበት ፕሮግራሞች እንዳሉትም ጠቁመዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ዮናስ አረጋዊ በበኩላቸው የማስ ስፖርቱ ማህበረሰቡን የሚያቀራርብ እና ቤተሰባዊነትን የሚፈጥር ነው ብለዋል።

በአካልም ሆነ በአዕምሮ ጠንካራ የሆነ ትውልድ እንዲፈጠርም የዚህ መሰል የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎች ባህል መሆን እንዳለባቸውም በማሳሰብ።

የማስ ስፖርቱ በቀጣይ ጊዜያት በወረዳዎችና  በየክፍለ ከተማው ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ እንደሚደረግም ኮሚሽነሩ አሳውቀዋል።

በዛሬው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በርካታ ቁጥር ያለው ማህበረሰብ ተሳትፈዋል።