ኢንደስትሪው የሚፈልገውን የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፍራት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተገለፀ

69
ጥቅምት 9/2012 በጋምቤላ ክልል የኢንደስትሪ ልማቱ የሚፈልገውን ብቃት ያለው የሰለጠነ የሰው ኃይል ለማፈራት የክልሉ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት ጠንክረው ሊሰሩ እንደሚገባ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አሳሰቡ። በክልሉ ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ችግሮችና መፍትሄዎች ዙሪያ ያተኮረ የውይይት መድረክ በጋምቤላ ከተማ ተካሄዷል። ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ኡሞድ ኡጀሉ በመድረክ ላይ እንደገለጹት ከቴክኒክና ሙያ ስልጠና በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ ለተጀመረው ልማት የሚያስፈልገውን የሰለጠነ የሰው ኃይል በማፋራት ረገድ ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው። በተለይም ከግብርና ወደ ኢንደስትሪ መር ኢኮኖሚ ለመሸጋገር የተነደፈውን ግብ የሚያሳካ መካከለኛ ደረጃ የሰለጠነ የሰው ኃይል ማፍራት የሚቻለው በቴክክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት መሆኑን ተናግረዋል። ይሁን እንጂ በክልሉ በሚገኙ የቴክኒክና ሙያ ማስልጠኛ ተቋማት ዘመኑ የሚጠይቀውን የሰው ኃይል በጥራትም ሆነ በብዛት በማፍራት ረገድ ውስንነቶች እንዳለባቸው ገልጸዋል። ለዚህም ዋነኛው ምክንያት የህብረተሰቡ ግንዛቤ ማነስ፣ ተቋማቱ በበቂ የሰው ኃይልና ግብዓት ያለመደራጀት ተጠቃሽ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም በተቋማቱ የሚታዩ ችግሮችን በመፍታት ብቁና ስራ ፈጣሪ ዜጋ በብዛትና በጥራት ለማፍራት ተቋማቱ ጠንክረው ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል። የክልሉ መንግስት ለዘርፉ መጠናከር የሚያሰፈልገውን ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑንም ርዕሰ መስተዳደሩ ገልጸዋል። የክልሉ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡኩኝ ኦኬሎ በበኩላቸው  በዘርፉ የሚፈለገውን የሰው ኃይል ለማፍራት የሁሉንም አካላት የተቀናጀ ጥረት እንደሚጠይቅ ተናግረዋል። በተለይም የክልሉ ወጣቶች ከመንግስት ስራ ጠባቂነት አስተሳሰብ ሊወጡ ባለመቻለቸው በዘርፉ የመሰልጠን ፍላጎት እንደሌላቸው ገልጸዋል። በመሆኑም ለዘርፉ መጠናከር ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩሉን ሚና እንዲወጣ የጠየቁት ኃላፊው የውይይት መድረኩ ዓላማም የባለድርሻ አካላትን የአጋርነት ሚና ለማጠናከር ነው ብለዋል። ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል አቶ አንዳርጌ ዋሲሁን በሰጡት አስተያየት በክልሉ ሶስት የመንግስት የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት ቢኖሩም በበቂ ግብዓትና የሰው ኃይል  አልተደራጁም ብለዋል። በመሆኑም በዘርፍ ጥራት ያለው ባለሙያ ለማፈራት ተቋማቱን በበቂ የሰው ኃይልና ግብቶች ማደረጀት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡ የቴክኒክና ሙያ ማልጠኛ ተቋማት ብቃት ያለው ዜጋ ከማፍራት ባለፈ በቴክኖሎጂ ፈጠራም ተጨማሪ ኃላፊነት ይጠበቅባቸዋል ያሉት ደግሞ አቶ ገዛኸኝ ገብርሚኪኤል ናቸው። ስለሆነም ለዘርፉ መጠናከር ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ ተቀናጀቶ መስራት እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል፡፡ በጋምቤላ ከተማ ላለፉት ሁለት ቀናት በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ የክልሉን ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተሳታፊዎች ሆነዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም