በዱከም ከተማ አዲስ የተገነባው ዘመናዊ የቡና ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ተመረቀ

139
ጥቅምት 9/2012  በአሮሚያ ክልል ዱከም ከተማ በ120 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው ዘመናዊ የቡና ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ተመረቀ። በጉጂ ሃይላንድ ኮፊ ፕላንቴሽን ኩባንያ ተሰርቶ ለሥራ ዝግጁ የሆነው ፋብሪካው ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተመርቋል። ፋብሪካው ቡናን ለማቀነባበር ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ የሚጠቀም ሲሆን ከእጅ ንኪኪ ነጻ በሆነ መንገድ የቡና ፍሬን ከገለባ መለየት፣ ማበጠር፣ ባዕድ ነገሮችን ማስወገድና በጥራት ታሽጎ ለገበያ ማቅረብን ያካተተ ነው። የኩባንያው ሥራ አስኪያጅ አቶ ወዴሳ ያቺሲ እንደተናገሩት፤ ፋብሪካው ሰርቶ ለማጠናቀቅ ከሁለት ዓመት በላይ የፈጀ ሲሆን ለማቀነባበሪያ የሚያግዙ መሳሪያዎች ከውጭ እንዲገቡ ተደርጓል። የቡናውን ደረጃ ለመለየት ፋብሪካው ላብራቶሪ እንዲኖረው መደረጉን የገለጹት ሥራ አስኪያጁ ይህም ጥራት ያለው ቡና በማቅረብ ተወዳዳሪ ለመሆን የሚደረገውን አገራዊ ጥረት ያግዛል ይላሉ። ከአሁን በፊት በአገር አቀፍ ደረጃ ዘመናዊ የቡና ማቀነባበሪያ በበቂ መጠን አለመኖር በተለይ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ አስቸጋሪ እንደነበር አስታውሰዋል። እንደዚህ አይነት ዘመናዊ ፋብሪካዎች ወደ ሥራ መግባታቸው ግን ችግሩን ያቃልለዋል ብለዋል። እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ ፋብሪካው በሰዓት ብዙ ቶን ቡና የሚያጣራ በመሆኑ በአገር ደረጃ ያለውን የመጋዘንና የማበጠሪያ እጥረት ችግር የሚያቃልል ነው። ጉጂ ሃይላንድ ኮፊ ፕላንቴሽን የቡና ምርት ከራሱ እርሻ ከመሰብሰብ ባለፈ 700 ለሚሆኑ የጉጂ ዞን አርሶ አደሮች የገበያ ትስስር እንደሚፈጠር አቶ ወዴሳ አረጋግጠዋል። ኩባንያው በሚያከናውናቸው የኢንቨስትመንት ተግባራት በውጭ ምንዛሪ ለአገር ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ በተጨማሪ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል እየፈጠረም ነው። ለ140 ዜጎች ቋሚና ጊዚያዊ የሥራ ዕድል የሚፈጥር ይሆናል። የኦሮሚያ ገበያ ልማት ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር ወይዘሮ ገነት አብደላ እንደተናገሩት እንደዚህ አይነት ዘመናዊ ፋብሪካዎች እውን መሆናቸው ለዘርፉ ልማት ከፍ ያለ ሚና አለው። የቡና ማቀነባበሪያ ፋብሪካው ወደ ሥራ መግባቱ የአገሪቷ ዋነኛ የውጭ ምንዛሬ ማግኛ ሆነውን የቡና ምርት ተፈላጊነት እንዲጨምርም የሚያደርግ ነው። ኩባንያው ከኢንቨስትመንቱ ጎን ለጎን በመንገድና በትምህርት ግንባታ እንዲሁም መሰረተ ልማት አቅርቦት ላይ ከመንግሥት ጋር ተባብሮ በመስራት ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል። ከአንድ ሳምንት በፊት በአሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ሻኪሶ ወረዳ ደንበወዶ ቀበሌ በ2 ሚሊዮን ብር ወጪ ያስገነባው ትምህርት ቤትም የሚጠቀስ ነው። ከዚህ ባለፈም የኢኮኖሚ አቅም ለሌላቸው 206 ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉ ታውቋል።                                      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም