የአማራ ባንክ አክስዮን ማህበር ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ለምስረታ የሚያበቃውን ከግማሽ ቢሊዬን ብር በላይ ሰበሰበ

212

ጥቅምት 9 /2012 የአማራ ባንክ አክስዮን ማህበር ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የባንክ አገልግሎት በማቅረብ በክልሉ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት ለውጥ ለማምጣት እንደሚሰራ የባንኩ አደራጅ ኮሚቴ አስታወቀ።

ባንኩሁለትወርባልሞላጊዜውስጥለምስረታየሚያበቃውንከግማሽቢሊዬንብርበላይከአክስዮንሽያጭመሰብሰቡ ተመልክቷል።

ባንኩን ለማቋቋም እስካሁን የተካሄደውን የአክሲዮን ሽያጭ፣ አጠቃላይ የስራ እንቅስቃሴና የቀጣይ አቅጣጫ አስመልክቶ ትናንት በባህር ዳር ከተማ ውይይት ተካሄዷል፡፡

የአደራጅ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ መላኩ ፈንታ በውይይቱ ላይ እንደገለጹት ባንኩ የሰበሰበው ገንዘብ ለምስረታ የሚያበቃው ቢሆንም ለህዝብ በገባው ቃል መሰረት የአክስዮን ሽያጩን እስከ ህዳር ወር እንደሚቀጥል አስታውቋል።

ባንኩ ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከ15 ሺህ ህዝብ በላይ በማሳተፍ ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ከአክስዮን ሽያጭ መሰብሰብ መቻሉን ገልጸዋል።

በአክስዮን ሽያጩም 10 ባንኮች መሳተፋቸውን ጠቁመው ይህም ዝቅተኛውን የማህበረሰብ ክፍል ተደራሽ ለማድረግ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አስረድተዋል።

የአማራ ባንክ ዋና ዓላማ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የባንክ አገልግሎት በማቅረብ በክልሉ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት ለውጥ ለማምጣት መሆኑን ተናግረዋል።

በምክትል ርዐሰ መስተዳድር ማዕረግ የአማራ ክልል የኢንቨሰትመንትና የኢንዱሰትሪ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው የአማራ ባንክ አክስዮን ማህበር መመስረቱ ከባንክ ውጭ የሚንቀሳቀሰውን ገንዘብ ወደ ህጋዊ እንቅስቃሴ በማምጣት ለክልሉ ኢንቨስትመንት፣ ልማት እድገት በማዋል አጋዝ ሃይል እንደሚሆን እምነታቸውን ገልፀዋል፡፡

ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ወስጥ ለምስረታ የሚያበቃውን የተፈቀደ ገንዘብ መሰብሰቡ የአደራጅ ኮሚቴውን ጠንካራ እንቅስቃሴ የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በአማራ ባንክ አክስዮን ማህበር የፕሮጀክት ማኔጀር ወይዘሮ መሰንበት ሸንቁጤ በበኩላቸው ባንኩ ተጽእኖ ፈጣሪነትን፣ አትራፊነትን፣ ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠትንና ዘመናዊ ቴክኖሎጅ ተጠቃሚነትን የተላበሰ እንዲሆን በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡

በዚህም ”የአክስዮን ባለድርሻዎችና ሌሎች የባንኩ ተጠቃሚ ደንበኞች በኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ልማት ውጤታማ እንዲሆኑ ከማማከር ጀምሮ አስፈላጊውን እገዛ በማድረግ ለውጤት እንዲበቁ ሃላፊነቱን የሚወጣ ባንክ እንዲሆን ይሰራል” ብለዋል።

ከአማራ ክልል እስልምና ምክር ቤት የመጡት ሸክ ኡስማን ኡመር በበኩላቸው ባንኩ የሙስሊሙ ማህበረሰብ ከሃይማኖቱ አስተምህሮ አንፃር የሚገለገልበት አሰራር በማምጣት ሚናውን እንዲጫወት ጠቁመዋል፡፡

ባንኩ ሴቶችን በቁጠባ በማበረታትና ለኢንቨስትመንት የሚውል ብድር በማመቻቸት ከሌሎች ባንኮች በተለየ መልኩ አዲስና ጠቃሚ አሰራር ይዞ መምጣት እንዳለበት የገለፁት ደግሞ ከአማራ ክልል ሴቶች ማህበር የመጡት የውይይቱ ተሳታፊ ወይዘሮ አዲስ ጫኔ ናቸው።

ባንኩ በመጭው ህዳር ወር 2012 ዓ.ም የመጀመሪያ ጉባኤውን ለማካሄድ የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተካሄዱ መሆኑን ካባንኩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

ባንኩ የአክስዮን ሽያጭ ከጀመረበት ከነሃሴ ወር 2011 ዓ.ም ጀምሮ ባከናወነው እንቅስቃሴና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ባተኮረው ውይይት ላይ የአክሲዮን ባለድርሻዎች፣ የልማት ድርጅቶች፣ የተለያዩ ባንኮች ተወካዮችና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ተሳትፈዋል፡፡