የአዲስ አበባ መምህራን ማህበር በ176 ሚሊዮን ብር ወጪ ሆስፒታል ሊገነባ ነው

84
አዲስ አበባ ሰኔ 11/2010 የአዲስ አበባ መምህራን ማህበር በ176 ሚሊዮን ብር ወጪ ሆስፒታልና ሁለገብ ማዕከል ሊገነባ ነው። ማህበሩ ግንባታውን አስመልክቶ ባዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳለው ሆስፒታሉና ማዕከሉ በአዲስ አበባ ቤለር አካባቢ በሊዝ ባገኘው 3 ሺህ 600 ካሬ ሜትር መሬት ላይ ይገነባል። በ42 ወራት ውስጥ ይጠናቀቃል የተባለው ይህ ሆስፒታልና ሁለገብ ማዕከል 176 ሚሊዮን ብር የሚያስፈልገው  ሲሆን ወጪው በማህበሩና ከሌሎች አካላት በሚሰበሰብ ገቢ እንደሚሸፈን ተገልጿል። የአዲስ አበባ መምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ደበበ ገብረጻዲቅ ማህበራቸው ግንባታውን ለማከናወን በራሱ አቅም እንደማይችል አንስተው "ለመምህራኖቼ ሆስፒታል ይገባቸዋል" በሚል መሪ ሀሳብ በተለያዩ የገቢ ማግኛ መንገዶች ገንዘብ ለመሰብሰብ እቅድ እንደተያዘ ገልጸዋል። በዚህም መሰረት ከሰኔ 14 እስከ ሐምሌ 20 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ በተመረጡ ስድስት ቦታዎች እስከ 500 የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የሚሳተፉበት የንግድ ትርኢትና ባዛር እንደሚካሄድ ተናግረዋል። በባዛሩ ላይ ከሚሳተፉት አካላት የቦታ ኪራይ ገቢ ለመሰብሰብ መታቀዱንና በቀጣይ የንግድ ትርኢትና ባዛሩ በክልል ከተሞች ለማካሄድ እቅድ መያዙን አመልክተዋል። ከዚህ በተጨማሪም የግንባታውን ገጽታ የሚያሳይ በአምስት ብር የሚሸጥ አነስተኛ ሁለት ሚሊዮን ኩፖን የተዘጋጀ ሲሆን የመምህራንን ቀን በማስመልከት በአዲስ አበባና በተመረጡ የክልል ከተሞች መስከረም 25 ቀን 2011 ዓ.ም የአምስት ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫም ይካሄዳል። በአጠቃላይ ከሶስቱ የገቢ ማሰባሰቢያዎች ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ለማግኘት የታቀደ ሲሆን በቀጣይም ሌሎች የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሮች እንደሚካሄዱ በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳር ለዚህ ፕሮጀክት ግንባታ 20 ሚሊዮን ብር ድጋፍ እንዳደረገ ገልጸዋል። ሆስፒታሉና ሁለገብ ማዕከሉ ለእክምና አገልግሎት፣ለተለያዩ የማህበሩ ቢሮና የንግድ አገልግሎት እንዲሁም ለስብሰበና ለሲኒማ አዳራሽ አገልግሎት እንደሚውል አስረድተዋል። ሆስፒታሉ በነጻ ወይም አነስተኛ መጠን ባለው ተመጣጣኝ ክፍያ በዋነኛነት ለመምህራን ቀጥሎም ለሌሎች የህብረሰብ ክፍሎች አገልግሎት እንደሚውልም ነው አቶ ደበበ ያስረዱት። ለግንባታው የሚሆን የዲዛይን ስራ የተጠናቀቀ ሲሆን የግንባታ ተቋራጭና አማካሪ ለመለየት ጨረታዎች እየተጠናቀቁ መሆኑንም ጠቅሰዋል። ግንባታውም በመስከረም ወይም ጥቅምት ወር 2011 ዓ.ም ይጀመራል ብለን እንጠብቃለን ያሉት አቶ ደበበ የሚመለከተው አካል ለግንባታው ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል። የአዲስ አበባ መምህራን ማህበር በ1941 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን ከ19 ሺህ በላይ አባላት አሉት።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም