የደቡብ ክልል ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች የትልቅነት ማሳያዎች ናቸው :- የሰላም ሚኒስትር

261

ሀዋሳ  ጥቅምት  9/2012  የደቡብ ክልል ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ የመደመር እሳቤ ተቀምሮ ተግባራዊ ከመደረጉ አስቀድሞ በመደመር መንፈስ አንድ ሆነው ትልቅነትን ያሳዩ ህዝቦች መሆናቸውን የሰላም ሚንስትሯ አስታወቁ።

በጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተጻፈው ”መደመር ” መጽሀፍ ትናንት በሀዋሳ ተመርቋል።

በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ የተገኙት የደኢህዴን ሊቀመንበርና የሰላም ሚንስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል እንደተናገሩት የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝዝቦች ክልል ከመመስረቱ አስቀድሞ 21 ብሄራዊ ድርጅቶችን ያቀፈ አምስት ክልል ነበር።

በ1987 ዓ/ም ሃያ አንዱ ብሄራዊ ድርጅቶች ተባብረው በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ በመመስረት ተደምረው የዛሬውን የደቡብ ክልል መመስረት እንደቻሉ ተናግረዋል።

ይህ የመደመር እሳቤ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ተተንትኖ እንደ አንድ የፖለቲካ ፍልስፍና በጠቅላይ ሚንስትሩ ከመቅረቡ በፊት የደቡብ ክልል ተመስርቶ ወደ አንድነት ሲመጣ አብሮ በመቆም የሚኖረውን ሃይል ስለተገለጠልን ነው ብለዋል።

ይህንኑ የመደመር እሳቤ በጠቅላይ ሚንስትራችን ከአስር ዓመት በላይ ተረግዞ የቆየና በአጭር ጊዜ ውስጥ ተወልዶ ለውጥ ማምጣት ያስቻለ እንደሆነም ሚንስትሯ ጠቁመዋል።

መጽሀፍ መጻፍ ከባድ ነው ያሉት ሚንስትሯ “የሰው እርግዝና ጎረቤትም አይዞኝ ይላል ። ፈጣሪም ያግዛል ። የሀሳብ እርግዘና ግን ከባድ ነው ። የሀሳብ እርግዝናናን በተደራጀ መልኩ አምጦ መውለድ በመሪነት ያለን ከሳቸው ልምድ ልንወስድበት የሚገባ ነው” ብለዋል።

“መደመር ለኛ በዚህ መንገድ ተቀምሮ ፣ተተንትኖና ጎልብቶ ሲመጣ የበለጠ ሀሳቡን አፍታተን ከእኛ አንፃር ምን እንደሚጠቅመን በደንብ ተረድተን የበለጠ ወደፊት መሄድ የሚያስችል አቅምም ጉልበትም የሚፈጥር ስለሆነ ተነሳሽነቱ ትልቅ ክብርና ምስጋና የሚገባው ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

የሀዋሳ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ በበኩላቸው ኢትዮጵያውያን በልዩነት ውስጥ ጠንካራ አንድነት ያለንን ህዝቦች ነን ብለዋል።

አንዱ ከሌላው የተሳሰረና በርካታ የጋራ እሴቶች ያለን በመሆኑ ልዩነቶቻችንን በማጥበብ ከድህነት በፍጥነት ለመውጣት ለሚደረገው ርብርብ የጠቅላይ ሚንስትሩ የመደመር እሳቤን የያዘው መጽሀፍ ያለው ፋይዳ የጎላ እንደሆነ ገልጸዋል።

የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው በምረቃው ላይ ስለ መጽሀፉ ባቀረቡት ጽሁፍ እንዳሉት ኢትዮጵያውያን ረጅም ዘመን ያስቆጠረ የተለያየ ስርዓት ያለን ህዝቦች ነን።

በዓለም ጥንታዊ ታሪኮች ካላቸው ህዝቦች ገናና የነበርን ፣ በርካታ ታሪኮች ያሉንና አንድነትን መሰረት ባደረገ መልኩ አንድ ሀገር ሆነን ለዛሬ ደረጃ መብቃታችንን ተናግረዋል።

መንግስታዊ ቅርጽ ከመያዛችን አስቀድሞም ቢሆን በየራሳችን ባህላዊ አስተዳደር ስንመራ የኖርን ህዝቦች እንደነበርን ዛሬ ለትውልድ የተላለፉ ቅርሶቻቸን ያሳያሉ ብለዋል።

ዛሬ ላይ የደረስነው ያኔ የነበሩ ህዝቦች ተደጋግፈውና ተባብረው አንድነታቸውን ጠብቀው በመስራታቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ታዲያ ይህ ትልቅነትና ከፍታ የነበረን ህዝቦች እንዴት ወደኋላ ሊወርድ ቻለ የሚል እሳቤ ያደረባቸው ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከልጅነታቸው ጀምሮ የነበረውን እሳቤያቸውን በመቀመር በመጽሀፍ መልክ ሰጥተውናል ነው ያሉት።

አራተኛው የአቶ እርስቱ ንግግር መግቢያ 03፡17”እኛ ኢትዮጵያዊያን—ይመሰክራሉ “ መውጫ 04፡05

በመጽሀፉ ምረቃ ላይ የክልልና የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ አመራሮችና የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ተወካዮች ተሳታፊ ሆነውበታል።