የመደመር መፅሀፍ የለውጡ የርእዮተ ዓለም መመሪያ ሆኖ የሚያገለግል ነው

768

ሐረር ኢዜአ ጥቅምት 9 / 2012 ዓም  ”መደመር ” መፅሀፍ በእኩልነት ፣ በአብሮነት ፣ በነፃነትና በብልፅግና መንገድ የምንሰባሰብበት የለውጡ የርዕዮተ አለምና የተግባር መመሪያ ሆኖ ያገለግላል ሲሉ የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ተናገሩ ።
በኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የተፃፈው ”መደመር ” መፅሃፍ በሀረር ከተማ በክልሉ ባሕል መሰረት ትናንት በድምቀት ተመርቋል ፡፡

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተሰዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ባሰሙት ንግግር ”

”መደመር” መፅሃፍ ”የተከፋፈለና የተበታተነ አቋምና ፍላጎትን በማጥበብ የጋር ተጠቃሚነትን ለማረጋግጥ በእኩልነት ፣ በአብሮነት ፣ በነፃነትና በብልፅግና ጉዞ   የምንሰባሰብበት የለውጡ የርዕዮተ አለምና የተግባር መመሪያ ሆኖ የሚያገለግል በመሆኑ የላቀ ቦታና ትርጉም ሚሰጠው ነው ”፡፡መፅሃፉ በለውጡ ሂደት ሲስተዋሉ የነበሩ የግንዛቤና የጥልቀት ትንታኔ ሚዛን መዛባት ክፍተቶችን የሚሞላ ነው ብለዋል፡፡

በሰላም ፣ በፍቅር፣በይቅርታና በአንድነት እሴቶች የእርስ በርስ መደጋገፍና ጠንካራ አገራዊ ግብን የሚያሳካና የመደመር ሂደትና ፅንሰ ሃሳብ ለመረዳት፣ለመዋሃድና ለመተግበር መፅሃፉ የማይተካ ሚና ይኖረዋል ሲሉ ርዕሰ መስተዳደሩ ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም በለውጡ ላይ ያሉ የአመለካከትና የዝንባሌ ክፍተቶችን የሚሞላ በመሆኑ መላው የክልሉ ህብረተሰብ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥረትና ልፋት ውጤት የሆነውን የመደመር መፅሃፍ በማንበብ ለውጡ ቀጣይ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

በምረቃው ላይ ተገኝተው ስለ መፅሃፉ ማብራሪያ የሰጡት በጠቅላይ ሚኒስቴር ፅህፈት ቤት የፕሪስ ሴክረተሪያት ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን እንደተናገሩት ሀገራዊ አንድነትን ከመገንባትና ብሔራዊ መግባባትን ከማምጣት አንፃር መፅሀፉ በሀገሪቱ ያሉ ነባራዊ ሁኔታዎች ያገናዘበና ከዚህጋር በተያያዘ ያሉ ክፍተቶችን የሚሞላ ነው፡፡

በመድረኩ የተገኙ ተሳታፊዎች አንድነታችንን አጎልብተን ለውጡን ለማስቀጠል የሚረዳና ከጎረቤት አገራት ጋር ያለንን ግንኙትም የሚያጎለብት ነው ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል ፤

መፅሃፉ ከኖቤል ሽልማት አሸናፊነት ማግስት ለህዝብ መቅረቡ እንዳስደሰታቸውም  ተናግረዋል፡፡

በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ  የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኦርዲን በድሪና በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የፕሪስ ሰክረተሪያት ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ጨምሮ በክልሉ የሚገኙ የሃይማኖት አባቶችና ፣ የሀገር ሽማግሌዎች ፣ ወጣቶች ፣ ሴቶችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል ።

በእለቱም በአፋን ኦሮሞና በአማሪኛ የተፃፈው ”መደመር” መፅሃፍ በይፋ ለሽያጭ ቀርቧል፡፡