ለሲዳማ ህዝበ ውሳኔና ውጤት አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል…አቶ ርስቱ ይርዳው

284

ጥቅምት 9 /2012 የሲዳማ ህዝበ ውሳኔን ተከትሎ በዞኑና በክልሉ የሚኖሩ ህዝቦችን መብት ታሳቢ ያደረጉ ስራዎችን ለማከናወነ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ርስቱ ይርዳው ገለጹ።

ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ ትላንት ማምሻውን በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት በክልሉ ከክልል፣ዞንና ወረዳ አደረጃጀት ጋር በተያያዘ ይነሱ የነበሩ ግጭቶች ወደ ሰላም ተመልሰዋል።

ከክልል ዞንና ወረዳ መዋቅር ጋር በተያያዘ ከተለያዩ አካባቢዎች እየተነሳ እንደሚገኘውን ጥያቄ ለመመለስም ደኢህዴን አንደ ድርጅት ያስጠናውን ጥናት መሰረት ባደረገ መልኩ ህዝባዊ ውይይቶች እየተካሄዱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በክልሉ ምክር ቤት ጉባኤ ላይም በሲዳማ ህዝበ ውሳኔ አተገባበርና ውጤቱ ላይ በትኩረት የተመከረበት መሆኑን ጠቁመው እንደ መንግስት ህዝቡ ዘላቂ ጥቅሙን በሚያስከብርበት መንገድ ላይ ተወያይቶ እንዲወስን የሚደረግበት ሁኔታ መመቻቸቱንም አስታውቀዋል።

ህብረተሰቡ በአሁኑ ወቅት የክልሉንና የአካባቢውን ሰላም ለማስጠበቅ እያከናወነ ያለውን ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበው በሲዳማ ክልልነት ጥያቄ ዙሪያ የሚካሄደው ህዝበ ውሳኔ በሰከነና ሰላማዊ እንዲሆን የክልሉ መንግስት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

“ምርጫ ቦርድ ከህዝበ ውሳኔው አስቀድሞ የክልሉ ምክር ቤትና የሲዳማ ዞን አስተዳደር በሽግግር ጊዜው በንብረት ክፍፍልና ሲዳማ ክልል ሆኖ እንዲደራጅ ቢወሰን በዞኑ የሚኖሩ ሌሎች ብሄረሰቦችና ህዝቦች እጣ ፈንታ ላይ መክራችሁ አምጡ ባለው መሰረት የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል” ብለዋል።

በዚህም ውጤቱን ተከትሎ ሲዳማ ክልል ሆኖ ቢመሰረት የሽግግር ጊዜ ገደቡ አስር ዓመት እንዲሆን መወሰኑንና ይህ የሽግግር ጊዜ ጤናማና በሁለቱ ክልሎች መካከል አጋርነት እንዲኖር የሚያደርግ እንደሆነም አቶ ርስቱ አስታውቀዋል።

የንብረት ክፍፍሉም በሁለቱ ክልሎች መካከል ለዘመናት የነበረውን አብሮነትና አንድነት በማይሸረሽር የግልጽነትን መርህ መሰረት ባደረገ መልኩ እንደሚከናወን ገልጸዋል።

እንዲሁም ሌሎች ብሄረሰቦችና ህዝቦችን በተመለከተም በህገ-መንግስቱ መሰረት በማንኛውም ስፍራ ተንቀሳቅሰው ሰርተውና ንብረት አፍርተው የመኖር መብታቸው እንደሚከበር ተናግረዋል።

ህዝበ ውሳኔው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ርስቱ ይርዳው ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ከአስተዳደራዊ መዋቅርና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ባጋጠመው ግጭት በህይወትና በንብረት ላይ በደረሰው ጉዳት እጃቸው እንዳለ የተጠረጠሩ አካላት ጉዳይ በህግ እየታየ መሆኑን አስረድተዋል።

ክልሉ አሁን ላይ ወደ ቀደመ ሰላሙ መመለሱን የገለጹት አቶ ርስቱ ንብረት የወደመባቸውን አካላትም መልሶ የማቋቋም ስራ በቅንጅት እየተከናወነ እንደሚገኝም ተናግረዋል።