ፖለቲካና የህግ ማስከበር ተግባር  መቀላቀል  ለሰላም እጦት መንስኤ እየሆነ ነው … ምሁራን

177
ኢዜአ፤ጥቅምት 8/2012 የፖለቲካና የህግ ማስከበር ተግባራት መቀላቀል በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ለሚፈጠሩ የሰላም እጦት መንስኤ  መሆኑን  ምሁራን ተናገሩ። ኢዜአ ያነጋገራቸው ምሁራን እንዳሉት ኢትዮጵያ የብሄር፣ የሀይማኖትና የአመለካከት ብዝሀነት መገለጫ ብትሆንም ፖለቲካና የህግ ማስከበር ተግባራት መቀላቀል ለሰላም እጦት መንስኤ እየሆነ ነው። በፖለቲካ ለውጥ  በሀገራት አለመረጋጋት መከሰቱ ተፈጥሮአዊ ነው ያሉት በኮተቤ ሜትሮ ፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የማኔጅመንት መምህር ዶ/ር ሀይለ ሚካኤል ሙሌ “ለውጦች እስኪረጉም ከበፊቱ የባሰ  አስደንጋጭ ና ሀገራትን አለመረጋጋት ውስጥ ሊከቱት ይችላሉ” ብለዋል። ሰላም ለማህበራዊ ግንኙነትና ለሀገር ህልውና መሰረት ነው ያሉት ደግሞ በኢትዮጵያ  የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂክ ጥናት ኢስቲትዩት  የስትራቴጂክ ጥናት  ኤክስፐርት አቶ አበበ አይነቴ ናቸው፡፡ “ሰላም በጠፋበት  ስርአት ውስጥ ጸጥታን ማስከበር የመንግስትን ሙሉ ትኩረት በመውሰዱ የሀገር ኢኮኖሚም ሆነ የዜጎች ህልውና አደጋ ላይ ይጥላል” ያሉት አቶ አበበ፤ ሰላም እንዲረጋገጥና የህዝቡ በነጻ የማሰብና የመንቀሳቀስ መብት እንዲረጋገጥ መንግስትም   ከፍተኛውን ሀላፊነት ሊወስድ እንደሚገባ ያስረዳሉ። ማንኛውም ህብረተሰብ  ለህግ የበላይነት መከበር መብትና ግዴታውን መወጣት  እንዳለበት የሚገልጹት ጠበቃና የህግ አማካሪ መልካሙ ኦጎ በበኩላቸው “የሀገር ሰላምና ጸጥታን ማስከበር የመንግስት ትልቁ ሀላፊነት በመሆኑ ይሄን አለማድረግ ሀገርን ለስርአት አልበኝነት፣ የነዋሪዎች ነጻነትንም ለአደጋ ያጋልጣል” ነው ያሉት። “ቀደም ሲል  በሀገራችን የነበረው አፋኝ ስርአት   በመከፈቱ፤ ሁሉም  የመሰለውን ሃሳብ  ያለ ገደብ መስጠቱ  ለስርአት አልበኝነት አጋልጧል” ያሉት ዶ/ር ሀይለ ሚካኤል፤ ይህም መንግስት  የክልሎችን ና የማህበረሰቡን ጥያቄዎች በሚገባ እንዳይመልስ  እንቅፋት እየሆነበት ነው ይላሉ። መንግስት  በእነዚህ  ጉዳዮች በመጠመዱ ከህዝብ ጋር በእቅዶች ዙርያ ግልጽ ውይይት  በማድረግ   ህዝቡ የሚሳተፍበትና  በትግስት የሚጠብቅበትን  አሰራር አለመዘርጋቱ  ለውጡን እንዲጠራጠር እያደረገ መሆኑንም ይጠቅሳሉ። “በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች አሁን  የሚታየውን  አለመግባባት ለመፍታት  ባህላዊና ሀይማኖታዊ ስርአትን በአግባቡ አልተጠቀምንም” የሚሉት አቶ አበበ፤ የመልካም አስተዳደርና በፍትህ መጓደል  ምክንያት ሰዎች  በመንግስት ተቋማት  እምነት ማጣታቸው  ለሰላም መደፍረስ መንስኤ  እንደሆነ ያስረዳሉ። የሀይማኖት፣የቋንቋና የባህል እንዲሁም  የብዝሀነት  መገለጫን ወደ መልካም አጋጣሚ  መቀየር እንደሚቻለው ሁሉ አለአግባብ መጠቀም ደግሞ ለግጭት መነሻ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡ “ሀይልን በመጠቀም ህግን ማስከበር  የመንግስት ሀላፊነት  ብቻ ነው” የሚሉት የህግ አማካሪው መልካሙ ኦጎ፤  ከዚህ በተጻጻሪ በአንድ ሀገር ውስጥ ከመንግስት ጋር በመገዳደር መብትን ለማስከበር መሞከርም ሆነ የመንግስትን ጸጥታ የማስከበር ሂደትን ማወክ ሀገርን ለአደጋ እንደሚያጋልጥም አስረድተዋል፡፡ ዜጎች መብታቸውን ለማስከበር በሚያደርጉት እንቅስቃሴ የሌሎችን መብት የማክበር ግዴታ እንዳለባቸው ሁሉ፤ የዜጎችን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብት በመጠበቅ ህግን ማስከበር ደግሞ  የመንግስት ተቀዳሚው ተግባር  መሆኑን ነው የገለጹት። ለሰላም መኖር መተማመን ዋነኛው ነው ያሉት አቶ አበበ፤ በቂምና በበቀል መጠፋፋት፣ በታሪክ በመጨቃጨቅ ለዛሬ ፍላጎት ከማዋልይልቅ በጎውን በመውሰድ ሌሎቹን በይቅርታ ማለፍ  እንደሚገባም መክረዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም