”የመደመር ፍልስፍና ለዜጎች እኩል ተጠቃሚነት ጥያቄዎች ምላሽ ይሰጣል” ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ

356

ጋምቤላ፤ኢዜአ፤ ጥቅምት 8/2012የመደመር ፍልስፍና ለዜጎች እኩል ተጠቃሚነት ጥያቄዎች ምላሽ እንደሚሰጥ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ገለጹ፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድ የተጻፈው የመደመር እሳቤ ፍልስፍና መጽሐፍ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተመርቋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በምረቃው ሥነ ሥርዓት ላይ እንደገለጹት መጽሐፉ ለዜጎች ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥያቄዎች ምላሽ ይሰጣል።

ይህም የአገሪቱን ሕዝቦች አንድነትና አብሮነት የሚያጠናክርና እኩል ተጠቃሚነታቸውን ያረጋግጣል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የቀደምት ሥልጣኔ ባለቤት ብትሆንም፤ በተለያዩ የመንግሥት ሥርዓቶች የሥልጣን ዕድሜያቸውን ለማራዘም ሲጠቀሙባችው በነበሩት ርዕዮተ ዓለም አገሪቱ ከማደግ ይልቅ ወደ ኋላ ስትመለስ መቆየቷን ተናግረዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሀገሪቷ የነበሩባትን ፈጠና ተሻግራ በለውጥ ጎዳና ላይ የምትገኝ ብትሆንም፤ ተስፋዋን ለማጨለም የሚሞክሩ ፈተናዎች እንዳጋጠሟት አቶ ኡሞድ ገልጸዋል፡፡

በተለይም ለአገሪቱ ፈተና እየሆኑ የሚገኙት ጽንፈኝነት፣ብሔርተኝነት፣ አግላይነትና ግላዊነት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የመደመር እሳቤ አገሪቱን ወደ ተሻለ ብልጽግና ከመምራቱም ባለፈ የሕዝቦችን እኩል ተጠቃሚነት እንደሚያረጋግጥ ርዕሰ መስተዳድሩ አስረድተዋል፡፡

መጽሀፉ ከአሁን በፊት የተሰሩ ስህተቶችን በማረም ለመጪው ትውልድ ጥቅምና ፍላጎቱን ለማሳካት እንደሚያስችለው እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡

መጽሐፉ የመደመር ፍልስፍናን በማጠልሸት ለግል የፖለቲካ ጥቅማቸው ለሚንቀሳቀሱ አካላት ምላሽ እንደሚሰጥ ርዕሰ መስተዳድሩ አመላክተዋል፡፡

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር የመሠረተ ልማትና የከተማ ልማት አማካሪ ሚኒስትር አቶ ጃንጥራር አባይ እንዳብራሩት መጽሐፉ የአገሪቱን ሕዝቦች አንድነት በማጠናከር አገራዊ ለውጥ ወደፊት የማራመድ እሳቤን የያዘ ነው።

ከመድረኩ ታዳሚዎች መካከል አቶ ኡቶው ኡኮት በሰጠት አስተያየት የመደመር ፍልስፍና ዜጎች በአገራቸው ጉዳይ እኩል የመወሰንና የልማት ተጠቃሚነት መብትን ያረጋግጣል ብለዋል ።

ከአሁን በፊት የነበረው አሰራር በተለይም ጋምቤላን ጨምሮ ታዳጊ የሚባሉ ክልሎችን በአገራቸው ጉዳይ ላይ የመወሰን ዕድልን ነፍጎ መቆየቱን ተናግረዋል።

ዜጎች በመደመር ፍልስፍና ላይ የጠራ ግንዛቤ እንዲኖራቸው መሰራት እንዳለበትም ጠይቀዋል።

‘አገሪቱ እስካሁን ስትመራ የነበረው ከሌሎች አገራት በተቀዳ ርዕዮተ-ዓለም እንደነበር የገለጸው ደግሞ ሌላው ታዳሚ ወጣት ብርሃኑ እምሬ ነው።

አሁን ላይ ግን በዶክተር ዓቢይ የተጻፈው አገር በቀል የመደመር ፍልስፍና የአገሪቱን ማህበራዊ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ መቅረቡ የሚያስደስት ነው ብሏል።

በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የክልሉ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎችና  የመንግሥት ሠራተኞች ተገኝተዋል።