የቮሊቦል ተተኪ ስፖርተኞች አለመኖራቸው የቮሊቦል ስፖርት እንዲዳከም እያደረገው መሆኑ ተገለፀ

146

ጥቅምት 08/2012 የቮሊቦል ተተኪ ስፖርተኞች አለመኖራቸው የቮሊቦል ስፖርት እንዲዳከም እያደረገው ነው ተባለ።

ተተኪዎችን ለማፍራት የታዳጊ ወጣቶች የስልጠናና ምልመላ ስርአት ሊፈተሽና ባለድርሻ አካላትን በጋራ የሚሰሩበት ሁኔታ መመቻቸት እንደሚገባውም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን 20ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ዛሬ በአዲስ አበባ አካሄዷል።

የደቡብ ክልል ቮሊቦል ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ምትኩ ዳኢሞ በኢትዮጵያ የቮሊቦል ስፖርት የተተኪ ተጫዋቾች አለመኖራቸው በስፖርት ውስጥ የሚታይ ትልቁ ችግር ነው ብለዋል።

በሁለቱም ጾታዎች አሁን ያሉ ተጫዋቾች ረጅም ጊዜ የቆዩ ነባር ተጫዋቾች መሆናቸውንና ታዳጊ ወጣት ተጫዋቾችን በክለቦች በክልሎች እየታዩ አለመሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ከወዲሁ በታዳጊዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ካልተቻለ ነባሮቹ ጨዋታ ሲያቆሙ አዳዲስ ተጫዋቾችን ማግኘት አዳጋች በመሆኑ ጉዳዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ገልጸዋል።

የመዳወላቡ ዩንቨርስቲ የቮሊቦል ክለብ አሰልጣኝ አቶ ተፈሪ በላቸው በየክልሉ የቮሊቦል የፕሮጀክት ጣቢያዎች ቢኖሩም በሚባል መልኩ ስራ እየተሰራባቸው አለመሆናቸውን አመልክተዋል።

ይህም የሆነበት ምክንያት የታዳጊ ወጣቶች የስልጠናና ምልመላ ስርአት የቅንጅት አሰራርና ትስስር ባለመኖሩና ሙያው ያላቸው ሰዎች በምልመላና ስልጠና እየተሳተፉ ባለመሆናቸው ነው ብለዋል።

ያለውንም ችግር ለመፍታት የታዳጊ ወጣቶች የስልጠናና ምልመላ ስርአት መፈተሽና የቅንጅት አሰራር ስርአት መዘርጋት እንዳለበትም ጠቅሰዋል።

ክልሎችንና ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ያላቸውን ግንኙነት ማጎልበት፣ የሴት ክለቦችን ቁጥር መጨመር፣ ስፖርቱ ህዝባዊ እንዲሆን መስራትና የገቢ አማራጮችን ማስፋት የጠቅላላ ጉባኤው አባላት ያነሷቸው ጉዳዮች ናቸው።

የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ተክሉ ሸዋዬ የቮሊቦል የታዳጊ ወጣቶች ስልጠና ፕሮግራም ውጤታማ አለመሆኑን ፌደሬሽኑ ባለፈው ዓመት ባደረገው ጥናት ምልከታ አረጋግጧል ብለዋል።

ያሉት ችግሮች በጠቅላላ ጉባኤው አባላት የተነሱ መሆናቸውንና ፌዴሬሽኑ ይህንኑ ችግር ለመፍታት በተያዘው ዓመት በስፖርቱ እምቅ አቅም ያላቸው ክልሎች ተለይተው የታዳጊ ፕሮጀክት ስራ በትኩረት እንደሚሰራም ነው አቶ ተክሉ ያስረዱት።

የሴቶች ቮሊቦል ክለቦችን ከመጨመር አንጻር ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ እና ወላይታ ሶዶ ዩንቨርስቲ የሴት ክለብ እንዲያቋቅሙ መደረጉንና ይህም ተግባር በቀጣይ እንደሚኬድበት ተናግረዋል።

የሴቶች ቮሊቦል ስፖርት በአሁኑ ሰአት እየተዳከመ መምጣቱንና ዳግም እንዲያንሰራራ ሁሉም አካላት ከቃል በላይ በተግባር በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባቸውም ገልጸዋል።

ስፖርቱ ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረው የማደርግ ስራ በበጀት ዓመቱ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል ዋነኛው እንደሆነና ክልሎችና ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ያላቸው ግንኙነት እንዲጠነክርም ይሰራል ብለዋል።

የገቢ አማራጮችን ከማስፋት አኳያ የተጀመሩ አበረታች ስራዎች እንዳሉና ይሄም በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚሰራበትም አመልክተዋል።

የቮሊቦል ስፖርት ቀድሞ ወደነበረበት ዝና እንዲመለስ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በተቆርቋሪነትና በያገባኛል ስሜት በትጋትና በቁርጠኝነት መስራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል።

አሁን ያለው የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን ስር አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የአራት ዓመት ስራ ጊዜ የሚያበቃው በየካቲት 2012 ዓ.ም ነው።

በብሔራዊ የስፖርት ፌዴሬሽኖች የመተዳደሪያ ደንብ መሰረት የፌዴሬሽኖች የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የስልጣን ጊዜ እንዳለቀ አዲስ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት መመረጥ አለባቸው።

ነባሮቹ የፌዴሬሽን የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የስራ ጊዜ ከአራት ወራት በኋላ የሚጠናቀቅ በመሆኑ የስራ አስፈጻሚው ቆይታ በተመለከተ ጠቅላላ ጉባኤው ሀሳብ እንዲሰጥበት ጠይቀዋል።

የጠቅላላ ጉባኤው አባላት አሁን በስልጣን ላይ ያለው የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በ2012 ዓ.ም በጀት ዓመት የጀመረውን ስራ ጨርሶ በቀጣዩ በጀት ዓመት ምርጫው በሐምሌ ወር 2012 ዓ.ም እንዲካሄድ ጠይቀዋል።

ስራ አስፈጻሚው የስራ ጊዜው ሲጠናቀቅ ምርጫ ይካሄዳል እንጂ ጠቅላላ ጉባኤ ወስኖ ስራ እንዲቀጥል የፈለገውን የኮሚቴ አባል በስራው መቀጠል አይችልም የሚል ነገር የለውም ሲሉም አባላቱ አንስተዋል።

ጉባኤውን ሀሳቡን በማጽደቅ አሁን ያለው የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እስከ ሰኔ 30 ቀን 2012 ዓ.ም እንዲቆይ ወስኗል።

የፌዴራል የስፖርት ኮሚሽን የጉባኤውን ውሳኔ የሚያከብር ቢሆንም ደንቡ የሚለው መሰረት ምርጫ መሄድ ያለበት በመጋቢት ወር 2012 ዓ.ም እንደሆነ እንደሚያስቀመጥ ገልጿል።

ያም ቢሆን የስፖርት ኮሚሽኑ አመራር በጉዳዩ ላይ ተወያይቶ አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥም በጉባኤው ላይ ተገልጿል።

በጠቅላላ ጉባኤው የ2011 ዓ.ም እቅድ አፈጻጸም፣ የ2012 ዓ.ም እቅድ ሪፖርት፣ የ2011 ዓ.ም የኦዲት ሪፖርትና የባለፈው ዓመት ጠቅላላ ጉባኤ ቃለ ጉባኤ ውይይት ከተደረገባቸው በኋላ ጉባኤው በሙሉ ድምጽ አጽድቋቸዋል።

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን መተዳደሪያ ደንብ እንዲሁም የፋይናንስ፣የስልጠናና የስነ ምግባር መመሪያ የተደረጉ ማሻሻያዎች በጉባኤው በሙሉ ድምጽ የጸደቁ ጉዳዮች ናቸው።

የኢትዮጵያ የወንዶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ ህዳር 6 ቀን 2012 ዓ.ም የሴቶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ በታህሳስ 2012 ዓ.ም እንደሚጀመርም ተገልጿል።

የቮሊቦል ስፖርት በኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት ሲጀመር የውጭ አገራት መምህራን ስፖርቱን እንዳስጀመሩት በዘርፉ የተደረጉ ምርምሮች ያሳያሉ።

የስፖርቱ መዘውተርም በ1957 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቮሊቦል ፌዴሬሽን እንዲመሰረት አስችሏል።