“መደመር”በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ያሉ ልዩነቶችን በማጥበብ አንድነትን ያጠናክራል- የአሶሳ ነዋሪዎች

111

አሶሳ ጥቅምት 08 ቀን 2012 የጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ “መደመር” መጽሐፍ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ያሉ ልዩነቶችን በማጥበብ አንድነትን እንደሚያጠናክር የአሦሣ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

የከተማዋ አንዳንድ ነዋሪዎች ለኢዜአ እንደተናገሩት መጽሐፉ አገራዊ አንድነትን ለማረጋገጥ ያስችላል የሚል እምነት አላቸው።

ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ሽመልስ እንድሬ አገራዊ ለውጡ ከተጀመረበት ጊዜ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ መታየታቸው ይገልጻሉ።

ከነዚህም በጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ ተጽፎ ለምረቃ የበቃው መጽሐፍ በፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆነ በኅብረተሰቡ ውስጥ የሚታዩትን ልዩነቶች ለማጥበብ  ያስችላል  ብለዋል፡፡

”አገሪቱ አጥታው የቆየችውን ሃሳብ ይዞ የመጣ መጽሐፍ” ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩን መጽሐፍ ያደነቁት ደግሞ አቶ ባዬ ወዳይ የተባሉ ነዋሪ ናቸው፡፡

መጽሐፉ ኢህአዴግ ለዘመናት ሲከተል ከነበረው አግላይ አካሄድ ወጥቶ አካታች ለመሆን መዘጋጀቱን ያሳያል ባይ ናቸው፡፡

አቶ መሐመድ አማን የተባሉ ነዋሪ በበኩላው መጽሐፉ ከነ ልዩነቶቻችን በአንድነት ለአገር ለመቆም  እንደምንችል ያሳያል ይላሉ፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሐሰን መጽሐፉ ”ለአገራዊና ሕዝባዊ ህልውና ቀጣይነት አቅጣጫ የሚያሳይ ድንቅ አገር በቀል መመሪያ” ሲሉ አወድሰውታል፡፡

ዓለም ባደነቀው የመደመር ፍልስፍና የጀመርነው ለውጥ ከጫፍ ደርሶ ከድህነት እንድንወጣ ሁሉም ዜጎች መጽሐፉ ለያዛቸው ሐሳቦች ተግባራዊነት እንዲረባረቡ ጠይቀዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ አማካሪ አቶ ማሞ ምህረቱ ”አገራዊ ለውጡ የሚመራበት ፍኖተ ካርታ” ሲሉ መጽሐፉን ገልጸውታል፡፡

በመደመር እሳቤ የአገሪቱን ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና የውጭ ግንኙነት አቅጣጫዎች የሚያብራራው መጽሐፍ 280 ገፆች አሉት፡፡