በኢትዮጵያ ያሉት የብቅል ፋብሪካዎች የቢራ አምራቾችን 20 በመቶ ፍላጎት አያሟሉም

93
ጥቅምት 8/2012 በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የሚገኙት የብቅል ፋብሪካዎች የቢራ አምራቾችን 20 በመቶ ፍላጎት እንኳን ለማሟላት እያዳገታቸው መሆኑ ተገለፀ። ካለፉት ዓመታት ጀምሮ በኢትዮጵያ የተዘረጋውን ነፃ ገበያ መሰረት በማድረግ በርካታ የቢራ ፋብሮካዎች የተከፈቱ ቢሆንም ለቢራ ምርት ዋነኛ ግብኣት የሆነውን ብቅል የሚያቀርቡት የብቅል ፋብሪካዎች ግን ሁለት ብቻ ናቸው። በአሰላና በጎንደር የሚገኙት ብቸኛዎቹ የአገሪቱ የብቅል ፋብሪካዎች በመላው ሀገሪቱ ላሉት  የቢራ ጠማቂዎች እያቀረቡ ያለው ብቅል የፍጎታቸውን ከ20 በመቶ አይሞላም። በሀገሪቱ የብቅል ምርት ለማቅረብ የሚያስችል ተስማሚ አየርና በቂ የሆነ የሰው ሃይል ቢኖርም የሚፈለገውን ያሕል ምርት የሚያዘጋጁ ፋብሪካዎች እንደሌሉ የአሰላ ብቅል ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ አቶ አበራ መኮንን ለኢዜአ ተናግረዋል። በዚህም የተነሳ የአገሪቱ የቢራ ፋብሪካዎች 60 በመቶ የሚሆነውን የብቅል ገብስ ፍላጎታቸውን የሚያሟሉት በውጭ ምንዛሪ ከውጭ አገራት በማስገባት መሆኑን ገልፀዋል። የብቅል ፋብሪካ ካለመኖር ባሻገር ዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴን ያለመከተልና አርሶ አደሮች ለፋብሪካዎች የሚያቀርቡት የብቅል ገብስ በሕገ-ወጥ ነጋዴ መወሰድ ለአቅርቦቱ ዝቅተኛ መሆን የሚጠቀሱ ሌሎች ምክንያቶች ናቸው። እናም በዘርፉ የሚስተዋለውን የአቅርቦትና የፍላጎት ክፍተት በተወሰነ ደረጃ ለማቃለልም የአሰላ ብቅል ፋብሪካ የማምረት አቅምን የማሳደግ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ስራ አስኪያጁ ገልፀዋል። ፋብሪካው በአሁኑ ወቅት ያለውን 360 ሺህ ኩንታል የማምረት አቅም በአግባቡ ተጠቅሞ አቅርቦቱን እንዲያጠናክር ድጋፍ መደረጉን በመጠቆም። ከዚህም ሌላ የፋብሪካውን የማምረት አቅም  ወደ አንድ ሚሊዮን ኩንታል ለማሳደግ የሚያስችል  የአዋጭነት ጥናናት ተጠንቶ መጠናቀቁንም ገልፀዋል። ፋበሪካው ባካሄደው የአዋጭነት ጥናት መሰረት አቅሙን ለማሳደግ የሚያስችለውን የማስፋፊያ ግንባታ እንደሚያካሂድ ተናግረዋል። የመንግስት የልማት ድርጅት የነበረው የአሰላ ብቅል ፋብሪካ ከአንድ ዓመት በፊት ለኦሮሚያ የግብርና ሕብረት ስራ ማሕበራት ፌዴሬሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ ማሕበር በጨረታ ተላልፏል። ከዚህ ጊዜ ጀምሮም ፋብሪካው የተሻለ አፈፃፀም እያስመዘገበ መሆኑን አቶ አበራ ገልፀዋል። ገብስ አምራች አርሶ አደሩ ለፋብሪካው የሚያቀርበው የገብስ መጠን በእጅጉ መጠናከሩ ለአፈጻጸሙ መሻሻል አንዱ ምክንያት መሆኑንም አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም