በአዲስ አበባ የሚገኙ አብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች ከተቀመጠው ደረጃ በታች ናቸው

245

አዲስ አበባ ኢዜአ ጥቅምት 8/2012 በአዲስ አበባ ከሚገኙ ከቅድመ መደበኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ካሉ ትምህርት ቤቶች አብዛኞቹ ከተቀመጠው ደረጃ በታች መሆናቸውን የከተማ አስተዳደሩ የትምህርት ስልጠና ጥራት የሙያ ብቃት ምዘና ማረጋገጫ ባለስልጣን አስታወቀ።

በተደጋጋሚ ጥራታቸው ከተቀመጠው መስፈርት በታች የሆኑ 51 ትምሀርት ቤቶች ፈቃዳቸው ተሰርዞ እንዲዘጉ ተደርጓል።

ባለስልጣኑ በ2011 ዓ.ም በትምህርት ተቋማቱ ላይ ያደረገውን ምርመራ ይፋ አደርጓል።

በዚህም ወቅት የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሸዊት ሻንካ እንዳሉት፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 1233 የመንግስትና የግል ትምህርት ቤቶች ላይ የምርመራ ስራ አካሂዷል።

ከእነዚህ ውስጥ ደረጃቸውን አሟልተው የተገኙት 24 በመቶ ብቻ ሲሆኑ ቀሪዎቹ 76 ነጥብ 85 በመቶው በመንግስት ከተቀመጠው ደረጃ በታች መሆናቸውን ገልጸዋል።

”በከተማው የትምህርት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የተሻለ አፈጻጸም ቢመዘገብም የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ ፈታኝ ሁኔታዎች አሉ” ብለዋል።

የባለስልጣኑ የኢንስፔክሽን ቡድን መሪ አቶ መልካሙ ጸጋዬ እንደሚሉት፤ አብዛኞቹ የግል ትምህርት ቤቶች ከግብዓትና ከሂደት አንጻር ክፍተት ይታይባቸዋል።

የመማሪያ ክፍላቸውና ምድረ ግቢያቸው ለመማር ማስተማር ምቹ አለመሆኑ በፍተሻው ወቅት መረዳት ተችሏል።

በተጨማሪ ትምህርት ቤቶች በከፍተኛ ሁኔታ የሚታየው ችግር ስርዓተ ትምህርቱን ተግባራዊ አለማድረግ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በትምህርት ፖሊሲው ውስጥ ያልተካተቱና ስርዓተ ትምህርቱ የማያውቃቸው የተለያዩ የትምህርት ስርዓቶችን እየተጠቀሙ መሆኑን ገልጸው፤ ”ይህ መስተካከል አለበት” ብለዋል።

የመንግስት ትምህርት ቤቶች ደግሞ በውጤት ዝቅተኛ አፈጻጸም እንዳላቸው ጠቁመዋል።

ለዚህም መምህራን በተገቢው ሁኔታ ተግባራቸውን ያለመወጣትና ያለመከታተል ችግሮች መሆኑንም አመልክተዋል።

መንግስት በአሁኑ ወቅት የመንግስት ትምህርት ቤቶችን በከፍተኛ ሁኔታ እየደገፈ እንዳለ ማሳያዎችም መኖራቸው ተገልጿል።

በተደረገው የፍተሻ ስራ በተደጋጋሚ ጥራታቸው ከተቀመጠው መስፈርት በታች ሆነው የተገኙ 28 የቅድመ መደበኛ 20 የመጀመሪያ ደረጃ፣ 3 ሁለተኛ ደረጃ ትምሀርት ቤቶች ፈቃዳቸው ተሰርዞ እንዲዘጉ ተደርጓል።

ባለስልጣኑ ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ የትምህርት ተቋማት ላይ ምርመራ ሲያደረግ እንደነበር ተገልጿል።

በስነ ስርዓቱ ላይ የከተማው ምክር ቤት አባላት፣ የመንግስት ባለስልጣናት፣ መምህራንና ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

በአመቱ የላቀ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ትምህርት ቤቶች እውቅና ተሰጥቷል።