ውህደቱን በማጣጣል ያልተገባ ስያሜ ለመስጠት የሚደረግ ጥረት መሠረት የሌለው ነው… ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን

588

አሶሳ፤ ኢዜአ፤ ጥቅምት 08 / 2012  ሃገራዊ ለውጡን ለማስቀጠል ኢህአዴግ የጀመረውን ውህደት በማጣጣል ያልተገባ ስያሜ ለመስጠት የሚደረግ ጥረት መሠረት የሌለው መሆኑን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሃሰን አስታወቁ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ዛሬ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት ባለፉት 27 ዓመታት የተመዘገቡ ውጤቶች የመኖራቸውን ያህል ስህተቶችም ተፈጽመዋል፡፡

“በተለይም በሰብዓዊ መብትና ሌሎችም ዘርፎች የተፈጸሙ ስህተቶች ህዝብን ለትግል በማነሳሳት ለውጡ እንዲከሰት አድርጓል” ብለዋል ፡፡

የኢህአዴግ አባል እና አጋር ድርጅቶች ውህደት ለማድረግ የጀመሩት ጥረት ሃገራዊ ለውጡንና  የህዝቦችን አንድነት አጠናክሮ  ማስቀጠል እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡

ውህደቱ ለረጅም ዓመት በራሱ በኢህአዴግ ድርጅቶች እና አጋር ፓርቲዎች ሲነሳ የቆየ መሆኑን አውስተው የረጅም ጊዜ ጥናትን መሠረት ያደረገ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳመለከቱት ለውህደት ጠንካራ አቋም ተይዞ ወደ ሥራ ከተገባ ጀምሮ ክልሎችም ሆኑ አብዛኛው ህዝብ እየደገፈው ነው።

ሆኖም አንዳንድ ቡድኖች እና የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለይም የለውጥ ኃይሉ ውህደቱን እንደጀመረ አድርገው የሚሰጡ የተዛባ አስተያየት መሰረተ ቢስና ተገቢነት የሌለው መሆኑን  ገልጸዋል።

“እነዚህ ቡድኖች በተለይም ራሳቸው የኢህአዴግ አጋር ድርጅቶች ጠበቃ ለማስመሰል የሚያዳርጉት ጥረት አሳፋሪ ነው፤ በውህደቱ ሰነድ ዝግጅት ጀምሮ በንቃት የተሳተፍን በመሆኑ የውህደቱን ጠቀሜታ በሚገባ ተረድናል “ብለዋል፡፡

አሁን ያሉት የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች አደረጃጀት እንዳለ የሚቀጥል ከሆነ የተፈጸሙ ስህተቶች ላለመድገማቸው ዋስትና እንደሌለው አቶ አሻድሊ ተናግረዋል፡፡

“የፖለቲካ ድርጅት ከሀገር በላይ አይደለም “ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ የሃገርና የህዝብን ጥቅም ጥቂት ኃይሎች የሚወስኑበት አካሄድ ማክተሙን መረዳት እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

ህዝብን ብዥታ ውስጥ ለማስገባት ከሚያደርጉት ጥረት በመስከን ሊያስቡበት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በለውጡ የተገኙትን ቱሩፋቶች በመጠቀም ዴሞክራሲያዊ ውይይት በማድረግ ለሃገር የሚበጅ አካሄድ ሊከተሉ እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡