የፓርቲዎች ውሕደት ኢትዮጵያን ከፌደራል ስርአት ወደ አሐዳዊ ስርአት ለመመለስ ያለመ አይደልም- ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ

171
አዲስ አበባ ኢዜአ ጥቅምት 8/2012 በኢሕአዴግ ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ለማዋሃድ የተጀመረው ጥረት ኢትዮጵያን ከፌደራል ስርአት ወደ አሐዳዊ ስርአት የመመለስ ግብ የለውም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክትር ዓብይ አሕመድ ተናገሩ።
ዶክተር አብይ አሕመድ "መደመር" በሚል ርእስ ያሳተሙት መጽሐፋቸውን ዛሬ ባስመረቁበት ወቅት እንዳሉት የፓርቲው ውሕደትን እውን ለማድረግ የሚያስችለው ጥናት ለአንድ ዓመት ከስድስት ወራት ያህል ጊዜ ተጠንቶ የቀረበ ነው። በዚህም መሰረት የተጀመሩት ውይይቶች አሁንም ድረስ አለመጠናቀቃቸውን ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሆኖም አንዳንድ ወገኖች ውህደቱ አገሪቱን ከፌዴራል ወደ አሃዳዊ ስርዓት የመመለስና ሌላውን የመጨፍለቅ ግብ እንዳለው አድርገው የሚያቀርቡት ሀሳብ የተሳሳተ መሆኑን ጠቅሰዋል። የኢህአዴግ ፓርቲ አገሪቷን ወደ አሐዳዊ ስርአት የመመለስና የመጨፍለቅ ጉዳይን አስቦበትም ሆነ  አልሞት  የማያውቅ እሳቤ መሆኑንም አመልክተዋል። የፓርቲዎች መዋሃድን የሌላውን መጨፍለቅ አድርጎ መቁጠርም የተሳሳተ አስተሳሰብ መሆኑን የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በአንድ ገዢ የፖለቲካ ፓርቲ ስር እየተዳደሩ ያሉባቸውን የኢትዮጵያ ክልሎች ለአብነት በመጥቀስ አብራርተዋል። "የፓርቲው አንድ መሆኑ ኢትጵያን የሚጨፈልቅ ከሆነ፤ ሀገሪቷ አልነበረችም ማለት ነው፤ ምክንያቱም ህወሃት በሚመራው ትግራይ ውስጥ የሚገኙት የኢሮብና ኩናማ  ብሄረሰቦች አልተጨፈለቁም" ብለዋል። በተመሳሳይ በአማራ ክልልም ኦሮሞ፣ ቅማንት፣ አገውና አርጎባ የሚባሉ ሕዝቦች ክልሉን በሚመራው ብአዴን ሲተዳደሩ የቆዩ ሲሆን በዚሁ ፓርቲ ውስጥ ማእከላዊ ኮሚቴና ከፍተኛ አመራር ሆነው በፌዴራል ስርአት ውስጥ ኖረዋል። የደቡብ ክልሎቹ 56 ያህል ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችም ክልሉን ከሚመራው ደኢሕዴን ጋር በጋራ በመስራት ላይ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። እነዚህ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የተለያዩ ቋንቋዎቻቸውን እየተናገሩ በጋራ ሲሰሩ መቆየታቸውን የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ "አንድ ፓርቲ እነዚህን በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች ደምሮ ማስተዳደር ከቻለ፤ አንድ ፓርት ኢትዮጵያን ሲያስተዳድር አገርን መጨፍለቅ ሊሆን አይችልም" ሲሉም አስገንዝበዋል። በአሁኑ ዘመን ልዩነቶች የሚፈቱት በውይይት፣ አሸናፊ ሀሳብ በማምጣት መሆን ይኖርበታል የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "እኔ ያልኩት ካልሆነ እልቂት ይከተላል የሚለው አስተሳሰብ ጊዜ ያለፈበት ነው" ብለዋል። ከፓርቲዎቹ ውህደት ጋር በተያያዘ የተሻለና የብዙሃን ሀሳብ የሆነው ውሳኔ በቅርቡ ይፋ እንደሚሆንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል። ኢትዮጵያዊያን የተሻለ ሀሳብን የመቀበል አቅም አላቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ መላው የኢትዮጵያ ወጣቶች ከተሳሳቱ የፖለቲካ ቡድኖች እራሳቸውን እንዲከላከሉ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም