በደቡብ ሱዳን 200 ሺህ ሰዎች በጎርፍ ምክንያት ተፈናቅለዋል

133

ጥቅምት 8/2012 በደቡብ ሱዳን 200 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በጎርፍ ምክንያት መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ገለጸ።

ከባድ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ ካሁን በፊት ተከስቶ በማያውቅ ሁኔታ በደቡብ ሱዳን ሰሜን ምስራቅ አካባቢ 200 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች መጎዳታቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል።

የቻይና የዜና አውታር (ዥኑአ) እንደዘገበው በጎርፍ አደጋው በላይኛው የአባይ ተፋሰስ አካባቢ ባሉ ከ150 ሺህ በላይ የሱዳን ስደተኞች የሚገኙባቸው መጠለያዎችም ጉዳት ደርሶባቸዋል።

ጎርፉ ወደ ስደተኞች መጠለያ የሚያደርሱ ዋና መንገዶችን በማጥለቅለቁ ጤናን ጨምሮ ሌሎች መሰረታዊ አገልግሎቶችን ለማቅረብ አስቸጋሪ አድርጎታል ተብሏል።

ችግሩም የበሽታ የተጋላጭነትና ስርጭትን የሚያባብስ መሆኑን ያሳሰበው ኮሚሽኑ ደቡብ ሱዳን ባለፈው አመት ከኮሌራ ነጻ መሆኗን ብታውጅም አሁን የተከሰተው ጎርፍ ኮሌራን እንዳያስከትል ስጋት ፈጥሯል ብሏል።

በአሁኑ ወቅት ጉዳት የደረሰባቸው በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ በመሆናቸው የሰብአዊ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ተገልጿል።

የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ከ5 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ተጎጂዎች የቁሳቁስና ሌሎች ሰብአዊ እርዳታ ለማድረግ እየሰራ ቢሆንም ተጨማሪ እርዳታ እንደሚያስፈልግ ጥሪ አቅርቧል።

የኮሚሽነሩ መረጃ እንደሚያሳየው በምስራቅ አፍሪካ በግጭት ምክንያት ከተፈናቀሉ ሰዎች 300 ሺህ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ናቸው።

በተጨማሪም 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ህዝብ በደቡብ ሱዳን በተለያዩ አካባቢዎች በአገር ውስጥ ተፈላቅለዋል።