"መደመር" ያለፈውን መልካም ጥረት በመያዝና ስሕተቶችን በማረም የወደፊቱን የሚያመላክት አስተሳሰብ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ

131
ኢዜአ፤ ጥቅምት 8/2012 "መደመር" በኢትዮጵያ ያለፈውን መልካም ጥረት አጥብቆ የሚይዝ፣ በአገሪቱ የተፈፀሙ የትላንት ስሕተቶችን በማረም ወደፊቱን የሚያመላክት አስተሳሰብ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ገለፁ። በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተፃፈው "መደመር" መፅሃፍ ዛሬ በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ በተከናወነ ስነ-ስርዓት ተመርቋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር የመደመር አስተሳሰብ ነገን ያያል፣ ነገን ማሸነፍን ያልማል፣  በዚህም የወደፊቱን የብልጽግና ጉዞ ያመላክታል ብለዋል። "መደመር ኢትዮጵያውንም ቢያንስ የድሕነት ችግርን ለመጪው ትውልድ የምናሸጋግር ሳይሆን ብልጽግናን ለልጆቻችን የምናወርስ እንድንሆን የተግባር ንድፍን ጠቅልሎ የያዘ ነው" ሲሉም አመልክተዋል። በመደመር እሳቤ ልዩነት የለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ሆኖም ልዩነቶች ተከብረውና ጌጥ ሆነው ለአንድነት ምሶሶ መሆን ይችላሉ የሚል እምነትን ያራምዳል ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማከልም በአጠቃላይ የመደመር እሳቤ በቋንቋ፣ ባሕል፣ ሐይማኖትና ጾታ ረገድ የሚታዩ ልዩነቶች አንድ መሆንን የሚከለክሉ ሳይሆን ፀጋ ሆነው ለአንድነት ግርማ፣ ፍካትና ውበት ሊሆኑ ይችላሉ ብሎ በጽኑ ያመናል በማለት አብራርተዋል። ልዩነትን የሚያከብረው የመደመር አስተሳሰብ ችግሮችና ልዩነቶች የግጭትና ያለመግባባት ምክንያት እንዳይሆኑ ለአዳዲስ አማራጭ ሀሳቦች፣ ውይይትና ድርድር ቅድሚያ የመስጠት እምነትንም ይሰብካል  ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። በመደመር እሳቤ የትናንቱን ስሕተት እናርማለን የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላለፉት 28 ዓመታት ኢትዮጵያን የመራው ኢህአዴግ ሕገ -መንግስቱን በብዙ መንገድ ሲጥሰው መቆየቱን አንስተዋል። ኢህአዴግ አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማሕበረሰብ መፍጠር ግቤ ነው ሲል የነበረ ቢሆንም እስካሁን ኢትዮጵያን አንድ ማድረግ፤ እራሱም አንድ መሆን እንደተሳነው አመልክተዋል። ከፓርቲዎች ውህደት ጋር በተያያዘ ያላቸውን ሀሳብ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ 'ውህደት' የመደመር ፍልስፍና ከሆነና ኢህአዴግም ከተዋሐደ ወደእልቂት ይገባል የሚለው ሀሳብ የተሳሳተ መሆኑን አብራርተዋል። የፓርቲዎች መዋሃድን የሌላውን መጨፍለቅ አድርጎ መቁጠርም የተሳሳተ አስተሳሰብ መሆኑን የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በአንድ ገዢ የፖለቲካ ፓርቲ ስር እየተዳደሩ ያሉባቸውን የኢትዮጵያ ክልሎች ለአብነት በመጥቀስ አብራርተዋል። እንዲያም ሆኖ የመደመር አስተሳሰብን የማይቀበሉ አካላት "መባዛት" የሚል አማራጭ ይዞ መምጣትና  መሞገት ይገባልም ነው ያሉት።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም