ባለስልጣኑ ዘመናዊ የተሽከርካሪ ክብደት መጠን መቆጣጠሪያ ጣቢያዎችን አስገንብቶ ለአገልግሎት አበቃ

75
አዳማ ሰኔ 11/2010 የኢትዮዽያ መንገዶች ባለስልጣን በመንገዶች ላይ የሚደርሰውን ብልሽትና ጉዳት ለመቀነስ የክብደት መጠን መቆጣጠሪያ ጣቢያዎችን አስገንብቶ ለአገልግሎት ማብቃቱን አስታወቀ፡፡ ባለስልጣኑ ያስገነባቸውን ዘመናዊ የክብደት መጠን መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች ዛሬ አስመርቋል። በባለስልጣኑ የመንገድ ሀብት ማኔጅመንት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አለማየው አየለ በሞጆ ከተማ በተካሄደው የምርቃ ስነ ሥረዓት ላይ እንደገለጹት በአገሪቱ በከፍተኛ ወጪ የተገነቡ መንገዶች ከመጠን በላይ በጫኑ ተሽከርካሪዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ከጥቅም ውጭ እየሆኑ ነው። ይህን ችግር ለመፍታት ባለስልጣኑ ከጃፓን መንግስት ጋር በመተባበር ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ 14 ዘመናዊና ዲጂታል የክብደት መቆጣጠሪያ የምድር ሚዛኖችን መገንባቱን አስታውቀዋል። በአዲስ መልክ አገልግሎት መስጠት ከጀመሩት የክብደት መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች መካከል የሱሉልታ፣ ሆለታ፣ ሞጆ፣ ሰንዳፋ፣ ሻሻመኔ፣ አዋሽ፣ ኮምቦልቻ፣ ጅማና ደንገጎ ጣቢያዎች አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ገልፀዋል፡፡ ቀሪዎቹ የአለምገና፣ሰመራ፣ወረታ፣ጢቅና ከይሃ መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች ግንባታቸው ተጠናቆ መብራትና የውሃ መሰረተ ልማት እየተዘረጋላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የጃፓን መንግስት በሀገሪቱ የመንገድ ልማትና ጥገና እያደረገ ያለው ድጋፍ የሁለቱን ሀገራት ወዳጅነት ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑንም ገልጠዋል። በኢትዮዽያ የጃፓን አምባሳደር ምክትል መልዕክተኛ ሚስተር አኪራ ዑቺዳ  በበኩላቸው መንግስታቸው የኢትዮዽያን የመንገድ ልማትና ጥገና ሥራዎች በገንዘብና ቴክኒክ እየደገፈ መሆኑን ገልጠዋል። መንገድ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትና ዕድገት ቀጣይነት ወሳኝ መሆኑን ገልፀው ከመጠን በላይ በሚጭኑ ከባድ ተሽከርካሪዎች ምክንያት ለረዥም ጊዜ አገልግሎት መስጠት የሚችሉ መንገዶች ወደያውኑ የሚበላሹበት አጋጣሚ መኖሩንም ጠቁመዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በመንግስታቸው ድጋፍ የተገነቡት ዘመናዊና ዲጂታል የክብደት መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች በመንገዶች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ከመቀነስ ባለፈ ለጥገና የሚወጣውን ከፍተኛ ወጪ እንደሚቀንስ እምነታቸውን ገልፀዋል፡፡ ጣቢያዎቹ መንገዱን በአግባቡ ለመጠቀም ወሳኝ ሚና ያላቸው ከመሆኑም በላይ የመንገዶች ደህንነትና ዘላቂ አገልግሎት የሚያረጋግጡ መሆኑን አስረድተዋል። ኢትዮጵያ በሁለተኛው የልማት እቅድ የያዘችውን የመንገድ ልማትና ጥገና ሥራ መንግስታቸው በፋይናንስና በቴክኒክ እየደገፈ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ “የተገነቡት ዘመናዊና ዲጂታል የክብደት መቆጣጠሪያ ጣቢያዎች የድጋፉ አንዱ አካል ነው'' ብለዋል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም