ወባን ለመከላከል ሁሉም በቅንጅት መስራት አለበት...አቶ ኡሞድ ኡጁሉ

75
ኢዜአ ጥቅምት 7/2012፡- በጋምቤላ ክልል የወባ በሽታን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት ባለድርሻ አካላት በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አሳሰቡ። በክልሉ የክረምቱን መውጣት ተከትሎ ሊበራከት የሚችለውን የወባ በሽታ ለመከላከል በፓናል ውይይትና ህዝባዊ ንቅናቄ መድረክ በመፍጠር እየሰራ መሆኑን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታውቋል። የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በፓናል ውይይቱ ላይ ባስተላለፉት መዕልክት “በክልሉ ያለውን የወባ ስርጭት ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት የባለድርሻ አካላት ሚና መጠናከር አለበት” ብለዋል። በሽታው በተለይም በክልሉ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል። መንግስት በሽታውን ለመከላከልና ለመቀነስ ባለፉት ዓመታት ባከናወናቸው ስራዎች ከፍተኛ ለውጥ የመጣ ቢሆንም በክልሉ አሁንም የልማት እንቅፋት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የክልሉ መንግስት በሽታውን ለመከላከል ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳደሩ የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል። በክልሉ ጤና ቢሮ የጤና ማበልጸግና መከላከል የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ሪያንግ ፖች እንዳሉት ቢሮው በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው። በተለይም በክልሉ የክረምቱን መውጣት ተከትሎ ሊበራከት የሚችለውን የበሽታ ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር በህብረተሰቡ ዘንድ የፓናል ውይይትና የግንዛቤ ማስጨበጫ ዝግጅቶችን በመፍጠር ቢሮው እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የፀረ ወባ ኬሚካል ርጭት፡የወባ ትንኝ መከላከያ አጎበር ስርጭትና ሌሎች የመከላከል ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ እስከ አሁን ባለው ሂደት ከ103 ሺህ በላይ ቤቶች የፀረ-ወባ ኬሚካል ርጭት መደረጉንና በዚህም ከ300ሺህ የሚበልጡ የህብረተሰብ ክፍሎችን ከወባ በሽታ መከላከል እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡ በቀጣይም ጥረቱን በማጠናከር የበሽታውን ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡ ከፓናል ውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ወይዘሮ አጁሉ ኡቻር እንዳሉት የበሽታውን ስርጭት ለመከላከልና ለመቆጣጠር በህብረተሰቡ ዘንድ ከአጎበር አጠቃቀም ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮች ላይ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ መሰራት እንዳለበት ጠቁመዋል። በተለይም ህብረተሰቡ አጎበሩን ከታለመለት ዓላማ ውጪ ለሌሎች አገልግሎቶች የሚጠቀምበት ሁኔታ እንደሚታይም ትዝብታቸውን ተናግረዋል። በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተለይም የጤና ኤክስቴሽን ባለሙያዎች ለህብረተሰቡ በቂ የግንዛቤ መፍጠሪያ ስራ መስራት አለባቸው ያሉት ደግሞ ሌላው ተሳታፊ አቶ ኡዶል አጉዋ ናቸው፡፡ በክልሉ የወባ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጠጠር ያለመ የወባ መከላከል ሳምንት የፓናል ውይይቶችን ጨምሮ የተለያዩ ዝግጅቶች እየተካሔዱ ነው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም