የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የቻን የማጣሪያ የመልስ ጨዋታውን ነገ ከርዋንዳ አቻው ጋር ያደርጋል

179

ኢዜአ ጥቅምት 7/2012፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የ2020 የአፍሪካ አገሮች የእግር ኳስ ውድድር (ቻን) የመልስ ጨዋታውን ነገ ከርዋንዳ አቻው ጋር በኪጋሊ ያደርጋል።
በካሜሮን አስተናጋጅነት በጥር ወር 2012 ዓ.ም የሚካሄደውና በአገር ውስጥ ሊግ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ብቻ የሚሳተፉበት ስድስተኛው የአፍሪካ አገሮች የእግር ኳስ ውድድር (ቻን) ለመሳተፍ አገሮች የማጣሪያ ጨዋታቸውን እያደረጉ ይገኛል።

የውድድሩ የሁለተኛ ዙር የማጣሪያ መልስ ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ያደርጋሉ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመልስ ጨዋታውን ከርዋንዳ አቻው ጋር ነገ ከቀኑ 10 ሰአት በኪጋሊ በሚገኘውና 22 ሺህ ተመልካች በሚያስተናግደው ንያሚራምቦ ሪጅናል ስታዲየም ያደርጋል።

ሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች መስከረም 11 ቀን 2012 ዓ.ም በመቐለ ዓለም አቀፍ ስታዲየም ባደረጉት ጨዋታ ርዋንዳ 1 ለ 0 በሆነ ውጤት ማሸነፏ የሚታወስ ነው።

ዋልያዎቹ የመልስ ጨዋታቸውን ለማድረግ 20 ተጫዋቾችን ጨምሮ 29 ልዑካን በመያዝ ትናንት ወደ ርዋንዳ ኪጋሊ ያቀኑ ሲሆን ዛሬ ጨዋታው በሚካሄድበት ንያሚራምቦ ሪጅናል ስታዲየም ልምምድ ሰርተዋል።

ግብ ጠባቂው ጀማል ጣሰውና የክንፍ መስመር ተጫዋቹ አስቻለው ግርማ እንዲሁም የተከላካይ ክፍል ተጫዋቾቹ አህመድ ረሺድና ያሬድ ባዬ ባጋጠማቸው ጉዳት ምክንያት ወደ ኪጋሊ እንዳላቀኑ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በአሰልጣኝ አብርሃም መብራቱ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከርዋንዳ ጋር ላለበት የመልስ ጨዋታ ይረዳው ዘንድ ጥቅምት 2 ቀን 2012 ዓ.ም በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የአቋም መፈተሻ ጨዋታ ከዩጋንዳ አቻው ጋር አድርጎ 1 ለ 0 በሆነ ውጤት መሸነፉ ይታወሳል።

በአቋም መፈተሻ ጨዋታውም ብሔራዊ ቡድኑ ከፍተኛ የአጨራረስ ድክመት እንደታየበት ለመመልከት ተችሏል።

ዋልያዎቹ በቻን ውድድር ላይ ለመሳተፍ የርዋንዳ አቻውን በሁለት ጎል ልዩነት ማሸነፍ የሚጠበቅባቸው ሲሆን ግብ ለማስቆጠርም ያለውን የአጨራረስ ድክመት መቅረፍ ግድ ይላል።

ብሔራዊ ቡድኑ በመጀመሪያ ዙር የቻን ማጣሪያ ጨዋታ በሐምሌ ወር 2011 ዓ.ም ከጂቡቲ ጋር አድርጎ በድምር ውጤት 5 ለ 3 ማሸነፉ ይታወሳል።

በአንጻሩ በርዋንዳዊ ቪንሰንት ማሻሚ የሚሰለጥነው የርዋንዳ ብሔራዊ ቡድን ለመልሱ ጨዋታ ይረዳው ዘንድ ጥቅምት 3 ቀን 2011 ዓ.ም ኪጋሊ ላይ ከታንዛንያ አቻው ጋር ባደረገው ጨዋታ ያለ ምንም ግብ ጨዋታው በአቻ ውጤት መጠናቀቁ የሚታወስ ነው።

ከሜዳው ውጪ ዋልያዎቹን ያሸነፈው የርዋንዳ ብሔራዊ ቡድን በቻን ውድድር ላይ የመሳተፍ እድሉን ያሰፋ ሲሆን በነገው ጨዋታ አቻ መውጣትና ማሸነፍ በካሜሮኑ ውድድር ላይ ተሳታፊ ያደርገዋል።

በካሜሮን አስተናጋጅነት በጥር ወር 2012 ዓ.ም የሚካሄደው ስድስተኛው የአፍሪካ አገራት የእግር ኳስ ውድድር (ቻን) ውድድር ላይ ለመሳተፍ አገሮች የማጣሪያ ጨዋታቸውን ከሐምሌ ወር 2011 ዓ.ም ጀምሮ እያደረጉ ይገኛል።

በመጨረሻው ዙር የማጣሪያ ጨዋታዎች በደርሶ መልስ ውጤት የሚያሸንፉ 15 ብሔራዊ ቡድኖችና አስተናጋጇ ካሜሮን ጨምሮ 16 ብሔራዊ ቡድኖች በቻን ውድድር ላይ ይሳተፋሉ።