ስዊድን በኢትዮጵያ የሚደረጉ የምርምር ስራዎችን አግዛለሁ አለች

አዲስ አበባ ጥቅምት 7 /2012 የስዊድን መንግስት በኢትዮጵያ ለሚደረጉ የምርምር ስራዎች እገዛ ማድረጌን እቀጥላለሁ አለ። የአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት 50ኛ ዓመት የወርቅ እዮቤልዩ በዓል ዛሬ ተከብሯል። በመርሃ-ግብሩ በኢትዮጵያ የስዊድን አምባሳደር ቶርብዮን ፒተርሰን እና በኢትዮጵያ የኖርዌይ ኤምባሲ ተወካይ ኢግል ቶርሳስን ጨምሮ ሌሎች በጤናው ዘርፍ ያሉ ባለሙያዎች ተገኝተዋል። በኢትዮጵያ የስዊድን አምባሳደር ቶርብዮን ፒተርሰን እንዳሉት፤ ባለፉት 15 አመታት የስዊድን መንግስት ለአርማወር ሐንሰን የምርምር ማእከል የተለያዩ እገዛዎች ሲያደርግ ቆይቷል። የምርምር ኢኒስቲትዩቱ በኢትዮጵያና በአፍሪካ የምርምርና የህክምና የጥናት ማዕከል በመሆን እያገለገለ ይገኛል። "ስዊድን ለምርምር ተቋሙ እገዛ ባደረገችባቸው ዓመታት በርካታ ውጤቶችን አይተናል" በተለይ እንደዚህ አይነት የምርምር ማዕከል በኢትዮጵያ ማየት እጅግ የሚያበረታታ ውጤት ነው ብለዋል አምባሳደሩ። ግዙፍ የምርምር ማዕከልን መገንባት ብቻ ሳይሆን በብቃት ማስተዳደርና ባለቤት መሆንም ትልቅ ዋጋ አለው ሲሉም ተናግረዋል። እነዚህም በአገሪቱ የሚደረጉ ቁልፍ ዘርፎችን መደገፍ፣ "የደቡብ ለደቡብ ትብብር" በተባለ የትብብር መስክ ኢትዮጵያን ማገዝ እንዲሁም የባዮሜዲካል ድህረ-ምረቃ ትምህርትን ማገዝ ናቸው። የባዮሜዲካል የድህረ-ምረቃ ትምህርት የፒኤችዲ ተማሪዎች በስዊድናዊያን መምህራን እና ስዊድን በሚገኝ የምርምር ማእከል እገዛ የሚያገኙበትን ሁኔታ ማመቻቸትም ይገኝበታል። በተጨማሪም ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ የምትተገብራቸውን ተግባራት ስዊድን እንደምታደንቅም ተናግረዋል። በቀጥይም ስዊድን ለምርምር ተቋማት የምታደርገውን ድጋፍ አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል። አርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አበበ ገነቱ ኢንስቲትዩቱ በርካታ የፒኤችዲ ተማሪዎችን ያፈራ ነው ይላሉ። የባዮ-ሜዲካል ህክምና እና የሜዲካል ባዮ-ቴክኖሎጂ የምርምር ስራዎችን ማከናወን፣ በመቀመምና በማላመድ የህብረተሰቡን የተሻለ የህክምና አገልግሎት ጤናና ደህንነት ማረጋገጥ ላይ እንደሚሰራም ገልጸዋል። አዳዲስና የተሻሻሉ የህክምና ምርመራ ዘዴዎች ክትባቶችና መድኃኒቶች ላይ የህክምና የክሊኒካል ሙከራዎችን በማካሄድ የህብረተሰቡን ጤና ማሻሻል እንዲሁም በባዮሜዲካል ክሊኒካል እና በባዮ-ቴክኖሎጂ ምርምር ዘርፎች ላይ ለከፍተኛ የትምህርትና ለሌሎች መሰል ተቋማት የአቅም ግንባታ ስራ እንደሚሰራም ጠቅሰዋል። ተቋሙ በቀጣይም የሚያከናውነውን ጥናትና ምርምር በማሳደግ የጤና አገልግሎትን ይበልጥ ማሻሻል እንዲቻል በትኩረት እንደሚሰራም ገልጸዋል። አርማወር ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት በስዊድንና በኖርዌይ የልማት ድርጅቶች ድጋፍና በኢትዮጵያ መንግስት ትብብር በ1970 ዓ. ም የተቋቋመ ነው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም