ጎንደር ዩንቨርሲቲ የተመደቡ አዲስ ተማሪዎች አቀባበል ተደረገላቸው

95
ኢዜአ ጥቅምት 07/2012 ዓ.ም በጎንደር ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች የተደረገላቸው አቀባበል ትምህርታቸውን ተረጋግተው እንዲከታተሉ ተስፋ እንደሆናቸው በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አዲስ ገቢ ተማሪዎች ገለፁ፡፡ ዩኒቨርሲቲው በበኩሉ ተማሪዎች ራሳቸውን ለአደጋ ከሚያጋልጡ እንቅስቃሴዎች በመቆጠብና በመጠበቅ በትምሀርታቸው ውጤታማ ሆነው እንዲወጡ መትጋት እንዳለባቸው አሳስቧል፡፡ አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ አዲስ ገቢ ተማሪዎች መካከል ከአዲስ አበባ የመጣችው ተማሪ ራሄል በረከት እንደገለፀችው የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ከአፄ ቴዎድሮስ አየር ማረፊያ ጀምሮ በመቀበል ያለምንም እንግልት ወደ ግቢ ገብታለች፡፡ የዩኒቨርሲቲው አመራርና ተማሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና የከተማው ማህበረሰብ ያደረጉላቸው የእንኳን ደህና መጣቹሁ አቀባበል ትምህርቷን ተረጋግታ ለመማር ስንቅ እንደሆናትም ገልፃለች፡፡ ከኦሮሚያ ክልል የመጣ ተማሪ ሚኪያስ ረጋሳ በበኩሉ በተደረገላቸው አቀባበል ደስተኛ መሆኑን ገልፆ በቀጣይም ራሱን ከማኛውም ህገ- ወጥ ድርጊት በመቆጠብ ለትምህርት ብቻ ትኩረት እንደሚሰጥ ተናግራል። በተለይ በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ተዘጋጅቶ በወላጅ፤ በተማሪና በወረዳው ትምህርት ጽህፈት ቤት የተፈረመውን ሰነድ ተግባራዊ በማድረግ ለሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት መጠናከር የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ አስታውቋል፡፡ ልጃቸውን ወደ ዩኒቨርሲቲው ይዘው ከመጡ ወላጆች መካከል አቶ በረከት አዲሱ''አሁን ያየሁት ሰብአዊነት የተሞላው አቀባበል በልጄ ላይ ችግር ይደርሳል የሚል ስጋት እንዳይኖረኝ አድርጓል'' ብለዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ካሳው ተገኝ በበኩላቸው የዩኒቨርሲው የዘንድሮው የመማር ማስተማር ስራ  ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል ፡፡ በዩኒቨርሲቲው በዚህ ዓመት 5ሺህ አዲስ ተማሪዎች መመደባቸውን ገልፀዋል፡፡ የተመደቡ ተማሪዎችን በእውቀትና ክህሎት አንጾ ለማውጣትና ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደትን ለማስፈን ከፀጥታ አካላት፣ ከከተማው ህብረተሰብና ከጎንደር ልማትና ሰላም ሸንጎ አባላት ጋር ምክክር መደረጉን ተናግረዋል፡፡ በተለይ በዩኒቨርሲቲው የተጀመረው ''የቤተሰብ ፎረም'' የከተማ ነዋሪዎች አዲስ የሚገቡ ተማሪዎችን  እንደ ልጆቹ በማየት ክትትልና ድጋፍ የሚያደርጉበት አደረጃጀት በመሆኑ ለሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራ እገዛ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡ ተማሪዎችም ራሳቸውን ለአደጋ ከሚያጋልጡ እንቅስቃሴዎች በመቆጠብና በመጠበቅ በትምሀርታቸው ውጤታማ ሆነው እንዲወጡ መትጋት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው በዚህ ዓመት አዲስ የተመደቡ ተማሪዎችን ጨምሮ  ከ47 ሺህ በላይ ተማሪዎች በመደበኛና በተከታታይ የትምህርት ኘሮግራም በማስተማር ላይ መሆኑ ታውቋል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም