ከማዳበሪያ ብድር የተሰበሰብ ገንዘብ ያባከኑ ተቋማትና ግለሰቦች ላይ ጠንካራ እርምጃ ይወሰዳል

81
ሀዋሳ ኢዜአ ጥቅምት 07/2012 ዓ.ም  በደቡብ ክልል የአፈር ማዳበሪያ ዕዳ ገንዘብ ከአርሶ አደሩ ሰብስበው ያባከኑ ተቋማትና ግለሰቦች ላይ ጠንካራ እርምጃ እንደሚወሰድ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው ገለፁ ፡፡ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ የክልሉ ምክር ቤት የ2011 በጀት ዓመት ክንውን ላይ በመከረበት መድረክ እንደተናገሩት የሀገሪቱ ኢኮኖሚ የተመሠረተው በግብርና ላይ በመሆኑ  ያለፉትን ጊዜያት በሚያካክስ መልኩ ለዘርፉ እድገት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መረባረብ ያስፈልጋል ፡፡ ነገር ግን አሁንም የግብዐት ዕዳ የዘርፉ አይነተኛ ማነቆ መሆኑን ገልፀዋል ፡፡ ይህ ጉዳይ በግብርና እድገት ላይ ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶችን እየፈጠረ እንደሚገኝ ገልፀው በአቅርቦት ላይ ከፍተኛ ችግር እየፈጠረብን ነው ብለዋል ፡፡ እንደ አቶ ርስቱ ገለፃ ይህ የአፈር ማዳበሪያ ዕዳ ለሌላ ልማት የሚውል ሀብት እንዲባክን ከማድረጉም ባሻገር ኪራይ ሰብሳቢነት እንዲስፋፋ ምክንያት እየሆነ መምጣቱን ተናግረዋል ። የኪራይ ሰብሳቢነት መስፋፋት ደግሞ ለፀጥታ መደፍረስ የራሱ የሆነ አፍራሽ ተፅእኖ እየፈጠረ መሆኑን አስረድተዋል ። በዚህ ጉዳይ ላይ ያለ ምህረት መንቀሳቀስ ያስፈልጋል ያሉት አቶ ርስቱ የአፈር ማዳበሪያ ዕዳ ከአርሶ አደሩ ሰብስበው ያባከኑ በየደረጃው ያሉ ተቋማትና ግለሰቦችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠያቂ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል ፡፡ የክልሉ መንግስትም በዚህ ላይ ጠንካራ እርምጃ ይወስዳል ነው ያሉት ፡፡ በማስረጃ የተለዩ አጥፊዎች ለህግ እንዲቀርቡ የሚደረግ ሲሆን ያልተለዩትን ለመለየትም በግብረ-ኃይል አማካይነት የተጠናከረ ሥራ ይከናወናል ፡፡ ከዚህ ባሻገርም ሳይሰበሰብ የቀረውን ዕዳ አጠናቅቆ ለመሰብሰብ እስከ ታህሳስ ወር ድረስ ንቅናቄ በመፍጠር አንዲፈፀም ይደረጋል ። እንደ አቶ ርስቱ ገለፃ ክልሉ 4 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ የአፈር ማዳበሪ ዕዳ አለበት ፡፡ የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ እንደገለፁት ደግሞ ክልሉ በየወሩ 52 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ለዚህ ዕዳ ወለድ እየከፈለ ይገኛል ፡፡ ይህ ዕዳ መሰረዝ አለበት የሚል በዞንና ወረዳዎች ላይ ያለው አስተሳሰብ የተሳሳተ መሆኑን የተናገሩት አቶ ጥላሁን ግለሰቦችና ተቋማትን በፈፀሙት ችግር ልክ የማስጠየቅ ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል ፡፡ በቀጣይ ተግባራት ላይም የሁሉም አካላት ርብርብ እንደሚስፈልግ ነው ያመለከቱት ፡፡ የምክር ቤቱ አባል የሆኑት አቶ አየለ ላምቤቦ በበኩላቸው ክልሉ ያለበት የአፈር ማዳበሪ ዕዳ እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ ገለፀው እስከ ቀበሌ ያሉ የሚመለከታቸው ሴክተር መስሪያ ቤቶች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እየተወጡ ባለመሆኑ ዕዳው ሊወዘፍ መቻሉን ጠቁመዋል ፡፡ ሌላው የምክር ቤቱ አባል አቶ ታደለ ቡራቃ  ደግሞ ውዝፍ ዕዳው በሁሉም የክልሉ አካባቢ ላይ ወጥነት እንደሌለው ገልፀው ሴክተሩን የሚመሩት አመራሮች ቁርጠኝነት አናሳ መሆን እንጂ በህዝቡ ዘንድ ችግር አለ የሚል እምነት እንደሌላቸው ተናግረዋል ፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም