በጋምቤላ ክልል ሶስተኛው ምዕራፍ ዘላቂ የመሬት አያያዝና አጠቃቀም ፕሮጄክት ተጀምሯል

289

ጥቅምት 7 /2012   በጋምቤላ ክልል ዘላቂ የመሬት አያያዝና አጠቃቀምን በማስፋት ምርታማነቱን ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት ቅንጅታዊ ስራ መጠናከር እንዳለበት የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አስገነዘቡ፡፡

በክልሉ ከ90ሺህ በላይ የሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርገው ሶስተኛው ምዕራፍ ዘላቂ የመሬት አያያዝ ፕሮጄክት ተጀምሯል፡፡

የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በፕሮጄክቱ ማብሰሪያ ላይ እንዳሉት በክልሉ ዘላቂ የመሬት አያያዝና አጠቃቀምን በማስፋት ምርታማነቱን ለማሳደግ መንግስት በትኩረት እየሰራ ነው፡፡

በክልሉ ባለፉት ዓመታት የተከናወኑ ዘላቂ የመሬት አያያዝና አጠቃቀም ስራዎች የመሬቱን ለምነት ከማሳደግ ባለፈ የአርሶ አደሩን ምርታማነት እንዳሻሻለም ተናግረዋል፡፡

በተለይም በፕሮጄክቱ ምዕራፍ አንድና ሁለት ተጠቃሚ የሆኑ አርሶ አደሮች ህይወታቸውን በተሻለ መልኩ መምራት ከማስቻሉም በተጨማሪ ገቢያቸው ማደጉንም ጠቁመዋል፡፡

በመሆኑም በቀጣዩ ተግባራዊ የሚሆነው ፕሮጄክቱ የታለመለትን ግብ እንዲያሳካና የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ይበልጥ ለማሻሻል የሁሉም አካላት ቅንጅታዊ ስራ መጠናከር እንዳለበትም አሳስበዋል፡፡

የክልሉ መንግስት ለፕሮጄክቱ ውጤታማነት አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል በማድረግ በኩል በትኩረት እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡

የፕሮጄክቱ አስተባባሪ አቶ ሙላት ቢረጋ እንዳሉት ምዕራፍ ሶስት ዘላቂ የመሬት አያያዝ ፕሮጄክቱ በክልሉ በሚቆይባቸው አምስት አመታት በተመረጡ ሰባት ወረዳዎች ከ90 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል፡፡

በተለይም ፕሮጄክቱ በሚተገበርባቸው ዲማ ፣ ጎደሬ፣ መንገሺ፣ ኢታንግ፣ አቦቦ፣ ጋምቤላና መኮይ ወረዳዎች ከ77 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት እንዲያገግም ይደረጋል ብለዋል፡፡

ፕሮጄክቱ በመሬት አያያዝ፣ በደን ተከላ፣ በእንስሳት እርባታና በሌሎችም የስራ መስኮች ህብረተሰቡን በማሰማራት ገቢያቸውን እንዲያሻሽሉ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር በገጠር የሚገኙ ወጣቶችን በማደራጀት ወደ ስራ እንዲሰማሩ የማድረግ ዓላማ እንዳለውም ገልጸዋል፡፡

ለዚህም ለተያዘው በጀት ዓመት የስራ ማስፈጸሚያ 43 ሚሊዮን ብር መመደቡንና በቀጣይም አፈጻጸሙ እየተገመገመ የሚያድግበት ሁኔታ መኖሩን ተናግረዋል፡፡