ሞጆ ላይ እየተገነባ የሚገኘው የወጪና ገቢ እቃዎች ማስተናገጃ ደረቅ ወደብ ፕሮጀክት የዘርፉን አገልግሎት ያዘምነዋል ተባለ

204

ጥቅምት 7/2012 በ150 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጪ ሞጆ ላይ እየተገነባ የሚገኘው የወጪና ገቢ እቃዎች ማስተናገጃ ደረቅ ወደብ ፕሮጀክት ከዘርፉ አገልግሎት ጋር በተያያዘ የሚስተዋለውን ችግር በከፍተኛ መጠን እንደሚያቃልለው የማሪታይም ጉዳይ ባለስልጣን አስታወቀ።

የትራንስፖርት ሚኒስቴር ”የኢትዮጵያ ሎጅስቲክስ ትራንስፎርሜሽንና የኢንቨስትመንት እድሎች” በሚል ከባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ በአዲስ አበባ ውይይት አድርጓል።

በዚሁ ወቅት የማሪታይም ጉዳይ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን አበራ እንደገሉት፣ ከተጀመረ ሁለት ዓመታትን ያስቆጠረው ፕሮጀክቱ በአገሪቱ የሎጅስቲክስ ስርዓቱን ለማዘመንና በዘርፉ እያጋጠሙ ያሉትን ተግዳሮቶች ለመከላከል ያግዛል።

ፕሮጀክቱ የእቃዎችን የጅቡቲ ወደብ ላይ ቆይታ ለመቀነስ፣ ከባቡር ትራንስፖርት ጋር ተቀናጅቶ ምርትን በአገር ውስጥ ሙሉ በሙሉ በኮንቴነር አሽጎ ወደውጭ ለመላክና በአጠቃላይ በባህር ወደብና በሞጆ ደረቅ ወደብ መካከል ዘመናዊ አገልግሎት ለመዘርጋት ትልቅ ሚና አለው ሲሉም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ሎጂስቲክስድ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ዶክተር መንግስት ኃይለማሪያም በበኩላቸው 98 በመቶ የሚሆነው የአገሪቷ ገቢና ወጪ እቃዎች በሙሉ የሚስተናገዱት በሞጆ የደረቅ ወደብ በመሆኑ አገልግሎቱን ምቹ ለማድረግ ፕሮጀክቱ እንደተጀመረ ገልጸዋል።

በኢትዮ-ጂቡቲ የወደብ መተላለፊያ ውስጥ ትልቅ አገልግሎት የሚሰጥ በመሆኑ መሰረተ ልማትን ጨምሮ በአገልግሎት አሰጣጥና የወጪ ንግድን ለማቀላጠፍ ፕሮጀክቱ ያግዛል ብለዋል።

ከሁለት ዓመታት በኋላ ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀው ፕሮጀክቱ ጝንባታው በተያዘለት ጊዜ መሰረት በመካሄድ ላይ መሆኑም ተገልጿል።

በሌላ በኩል የአገሪቱን የሎጅስቲክ ዘርፍ ችግሮች ለመከላከል ያስችላል የተባለ የ10 ዓመት ብሄራዊ ሎጅስቲክስ እስትራቴጂ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል።

የዛሬ ዓመት ወደ ስራ የገባው ስትራቴጂው አገሪቷ በዘርፉ መጠቀም ያለባትን ያህል እንድትጠቀም ያስችላታል የሚል እምነት ተጥሎበታል።